የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በኮሌጁ ባገኘነው ተግባር ተኮር ስልጠና ሥራ ፈጣሪ ለመሆን የሚያስችል እውቀት እየጨበጥን ነው

May 16, 2025

IDOPRESS

ቦንጋ፣ግንባት 7/2017 (ኢዜአ)፦በኮሌጁ ባገኙት ተግባር ተኮር ስልጠና ከሥራ ጠባቂነት ሥራ ፈጣሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን ክህሎት እየጨበጡ መሆኑን የቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሰልጣኞች ተናገሩ።


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ በበኩሉ በክልሉ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ተግባራዊ ስልጠናን በማጠናከር ሰልጣኞችን የማብቃት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።


ከኮሌጁ ሰልጣኞች መካከል በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት የደረጃ-3 ሰልጣኝ ወጣት ዘካሪያስ አስራት በኮሌጁ የንድፈ ሀሳብ ዕውቀትን በተግባር መፈተሽ የሚያስችል ስልጠና እያገኘ መሆኑን ተናግሯል።


ስልጠናው በተግባር ተደግፎ መሰጠቱ ክህሎቱን በየጊዜው ለማሳደግ እንዳስቻለው ገልጾ፥ በስልጠናው ያገኘው እውቀት በቀጣይ ሥራ ጠባቂ ሳይሆን የራሱን ሥራ ለመፍጠር እንደሚያስችለው ተናግሯል።


በኮሌጁ የሆቴልና ቱሪዝም የትምህርት መስክ የደረጃ አራት ሰልጣኝ ውለታው አበቶ በበኩሉ፥ በመደበኛና በአጫጭር የሚሰጡ ተግባር ተኮር ስልጠናዎች እየወሰደ መሆኑን ተናግሯል።


በተቋሙ እየወሰደ ያለው ስልጠና የቀጣይ የህይወት ጉዞውን ለመወሰን የሚያስችል አቅም እየፈጠረለት መሆኑን ገልጿል።


በተግባር ተደግፎ ከሚሰጠው ስልጠና ያገኘውን እውቀት ተጥቅሞ ከሌሎች ጋር በመደራጀት የራሱን ሥራ ለመፍጠር ማቀዱንም ተናግሯል።


ሰልጣኞቹ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ በቀጣይ የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ስልጠናም እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።


የቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ተወካይና የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አስረስ ወልዴ በበኩላቸው፥በኮሌጁ በተግባር የተደገፈ ክህሎት መር ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።


በስልጠናው ለኢንዱስትሪው ብቁ የሰው ሃይል ከማፍራት ባለፈ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር፣ መቅዳትና ማሸጋገርን መሰረት አድርጎ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።


ሰልጣኞች ተመርቀው ሲወጡ የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ በስራ ፈጠራ ላይ አጫጭር የህይወት ክህሎት ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።


የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አብይ አንደሞ (ዶ/ር) በክልሉ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች፥ የአካባቢን ፀጋ መሰረት በማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጡ መሆነቻውን ተናግረዋል።


ሰልጣኞች እውቀት ብቻ ሳይሆን በቂ ክህሎት ኖሯቸው እንዲወጡ በተግባር የተደገፈ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ ወደ ኢንተርፕራይዝነት እንዲያድጉ እየተሰራ ነው ብለዋል።


በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በ20 የመንግስት ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ከሰባት ሺህ በላይ ሰልጣኞች በስልጠና ላይ እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.