የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ባለፉት የለውጥ አመታት አዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብ እና የትምህርት ቤቶችን አቅም ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት የሚደነቁ ናቸው

May 16, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ አመታት አዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብ እና የትምህርት ቤቶችን አቅም ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን መምህራንና የትምህርት አመራሮች ገለጹ፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራንና የትምህርት አመራር አባላት በመዲናዋ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

ኢዜአ ካነጋገራቸው መካከል የወርሃ የካቲት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በለጠ መኮንን፤ አዲስ አበባ ከተማ እንደ ስሟ ውብ ሆናለች ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሁሉ ሰው ተኮር መሆናቸውን በተግባር አረጋግጫለሁ ነው ያሉት፡፡

በተለይ በመንገድ፣ በመብራት፣ በመዝናኛና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሁም በትምህርት ቤቶች የተደረጉ የማሻሻያ እርምጃዎች ይበል የሚያስብሉ ናቸው ብለዋል፡፡

የጠመንጃ ያዥ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደሳለኝ ታዬ እንደገለጹት፤ የትምህርት ቤቶችን የመማር ማስተማር ስራ ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት አስደማሚ ናቸው፡፡

ትምህርት ቤቶች ላይ የተሰሩ ስራዎች ሁለንተናዊ ስብዕናው የተሟላ ትውልድ ከመገንባት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበርክታሉ ነው ያሉት፡፡

የአዲስ ምዕራፍ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር መዓዛ አበጋዝ፤ ካዛንችስ እንዳደጉ እና አካባቢው ለመኖር እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር አውስተዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ አምሮ እና ተውቦ በማየታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ጉዳት እንዳይደርስበት ሁላችንም ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል፡፡

የአዲስ ምዕራፍ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ኢፍቱ ኢብራሔም፤ በጉብኝቱ ወቅት ለትውልድ የሚሻገሩና በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው የልማት ስራዎችን አይቻለሁ ብለዋል፡፡


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር)፤ የጉብኝቱ ዓላማ መንግስት እያከናወናቸው ያሉ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ የልማት ተግባራትን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ብለዋል፡፡

በለውጥ ዓመታት አዲስ አበባን ውብና ጽዱ ከማድረግ በተጨማሪ የትምህርት ስብራቱን ለማከም በተወሰዱ እርምጃዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግስት ከሚወስዳቸው የትምህርት ቤት ማሻሻያ እርምጃዎች በተጨማሪ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከ10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የትምህርት ቤት ማሻሻያ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.