አዲስ አበባ፤ግንቦት 8/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በማፋጠን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የኢትዮጵያን ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ETEX 2025 በይፋ ከፍተዋል።
በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን ለዘላቂ ልማት፣ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ ብልጽግና ለመጠቀም በቁርጠኝነት እየሰራች ነው ብለዋል።
ኤክስፖው የቴክኖሎጂ ዕድገትን ከማሳየት ባለፈ የተለያዩ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበትና ትብብር የሚጠናከርበት መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን ያማከለ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ስትራቴጂ ነድፋ የተለያዩ ስራዎች እየሰራች መሆኑንም አንስተዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቴክኖሎጂ ልማት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በተለያዩ ዘርፎች ላይ በመጠቀም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑንም ነው ያነሱት።
ለአብነትም በግብርናና በጤና ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና የጤና አገልግሎትን ማዘመን መቻሉን አንስተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረጉ አንዱ ማሳያ ስማርት ሲቲ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንም የዜጎችን ኑሮ በማቃለል ዘመናዊነትን እያላበሰ ነው ብለዋል።
ወጣቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ በስፋት የሚሳተፉበት የ5 ሚሊዮን ኮደርስን ጨምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እውን ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነውም ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 እውን ለማድረግ የወጣቶችን ተሳትፎ በትምህርትና ስልጠና የበለጠ ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የቴክኖሎጂ ኤክስፖው እስከ ግንቦት 10/2017 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን የበርካታ ሀገራት ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችና ከአስር ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እየተሳተፉበት ነው።