አሶሳ፤ግንቦት 8/2017(ኢዜአ)፦የመኸር እርሻውን በኩታገጠም ዘዴና በቴክኖሎጂ ታግዘው ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአቡራሞ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመኸር እርሻ ዝግጅቱ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ነው።
በክልሉ አቡራሞ ወረዳ ማሳቸውን በትራክተር ሲያርሱ ያገኘናቸው አርሶ አደር ፈይሰል ኑረይን፥ ለመኸር እርሻው 20 ሄክታር የሚሆን ማሳ ለዘር ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነትን ለማሳደግና ሰብልን በጋራ ለመንከባከብ ያግዛል ያሉት አርሶ አደሩ፤ለሌሎች አርሶ አደሮችም ተሞክሯቸውን እያጋሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሌላው አርሶ አደር ፋንታሁን እጅጉ በበኩላቸው፥ 60 ሄክታር ማሳ ለማልማት ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በወረዳው በእስካአሁኑ እንቅስቃሴ 63 ሺህ ሄክታር ማሳ ለዘር የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአቡራሞ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አታላይ ደረጀ ናቸው።
ከዚህ ውስጥ 53 ሺህ ሄክታር የሚሆነው ማሳ በኩታ ገጠም የሚለማ መሆኑን ገልጸው፤አርሶ አደሩን ከባህላዊ አስተራረስ በማላቀቅ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እንዲላመድ በመድረጉ ምርታማነቱ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቁመዋል።
አርሶ አደሩ የግብዓት አቅርቦት እንዲያገኝ በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውሰው፥ በተለይም በዘር ብዜት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን፣ግብዓት ስርጭትና አቅርቦት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ተሰማ እንደተናገሩት፥ በዘንድሮው የመኸር እርሻ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በአሁኑ ወቅትም የማሳ ዝግጅቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው፥ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የኩታ ገጠም አስተራረስ ተመራጭ በመሆኑ አርሶአደሩ ተግባራዊ እያደረገው ነው ብለዋል።
አርሶአደሩ በትራክተር እያረሰ ነው ያሉት አቶ ፀጋዬ፣ይህም የእርሻ ማሳን ለማስፋፋት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልምዳቸውን ያሳድገዋል ነው ያሉት።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶአደሩ እና አልሚ ባለሃብቶች የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር ስርጭት እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው የመኸር እርሻ 55 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ትግበራ ተገብቷል።