አዲስ አበባ፤ ግንቦት 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ለማዘመን የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች የአመራሩን ሙያዊ ብቃትና የለውጥ ቁርጠኝነት አመላካች መሆናቸውን በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቲያን ክሪስቴንሰን ገለፁ።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
አምባሳደር ስቲያን ክሪስቴንሰን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሁለቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ትብብር አላቸው ብለዋል።
በተለይም በጤና፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ እንዲሁም በሌሎች መስኮች በጋራ እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ እያሳየች ያለውን ዘርፈ ብዙ ለውጥንም አድንቀዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች የአመራሩን ሙያዊ ብቃትና የለውጥ ቁርጠኝነት አመላካች መሆናቸውንም ነው አምባሳደሩ ያነሱት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንዲሁም ሚኒስትሮችና በየደረጃው ያሉ የመንግስት ኃላፊዎች ያላቸውን ትጋት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ሙያዊ ብቃትና የሥራ ተነሳሽነት ያላቸው ዜጎች ያሏት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ እዚህ በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያና ኖርዌይ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚሰሩ መሆኑንም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ሀገራት የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ትብብራቸውን የበለጠ ለማሳደግ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው እየሰሩ ይገኛሉ።