የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽነትን በማረጋገጥ በኩል ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ስራ አከናውናለች

May 26, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አካታች የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽነትን በማረጋገጥ በኩል ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ስራ ማከናወኗን የአይዲ ፎር አፍሪካ 2025 አመታዊ ጉባዔ ተሳታፊዎች ገለጹ።

አይዲ ፎር አፍሪካ 2025 አለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።


ጉባዔው በዲጂታል ማንነት ግንባታ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች የሚቀርቡበት ሲሆን በዲጂታል ፓስፖርትና መታወቂያ ላይ የተሻለ መፍትሄ ይዘው የመጡ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለእይታ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግና የጃፓኑ ቶፓን የጋራ ኩባንያ የሆነው ቶፓን ሴኪዩሪቲ የኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ቃልኪዳን አረጋ ኩባንያው በኢትዮጵያ የሚስጥራዊ ህትመቶችን ውስንነት ለመፍታት የተቋቋመ መሆኑን ይናገራሉ።

ኩባንያው ስትራቴጂክ የሆነውን ሚስጥራዊ ህትመት ከኢትዮጵያ ባለፈ ለሌሎች ሀገራት ተደራሽ ለማድረግ በኢትዮጵያ ግዙፍ የህትመት ፋብሪካ እየገነባ መሆኑንም አመልክተዋል።

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ በዓመት ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርት እንደሚያመርት ጠቅሰው፣ በዚህም ምርቱን ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች ሀገራት ለማቅረብ ያስችለዋል ብለዋል።

የፓስፖርት ህትመቱ በኢትዮጵያ መከናወኑ የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት ባለፈ ደህንነቱ የተጠበቀና ሀገራዊ እሴትን የተላበሰ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ የሚሆን ፓስፖርት ማቅረብ እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል።


የቻይና ኢፕቴክ ኩባንያ የሽያጭ ባለሙያ ሃርበርት ጎንዶ ኩባንያው አስተማማኝ የማንነትና ደህንነት ማረጋገጫ መፍትሄዎችን እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እያሳየች ያለው ለውጥ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው ኩባንያቸው ይህን ዕድል በመጠቀም በመላ ሀገሪቱ አገልግሎቱን ለማስፋት ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።

በሚስጥራዊ የፓስፖርትና ዲጂታል መታወቂያ ህትመት ስራ ላይ የሚሰራው የጀርመኑ ቬሪዶስ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዛቪየር ሮስት ኢትዮጵያ ዲጂታል ማንነትን ለማረጋገጥ በምትሰራው ስራ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት ብለዋል።


ኩባንያቸው ይህን ዕድል በመጠቀም በኢትዮጵያ ለመስራት ፍላጎት እንዳለውም ነው የተናገሩት።

በሚስጥራዊ ህትመት ስራ ላይ የተሰማራው ኢን ግሩፕ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አኜ ዲአሎ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ ባደረገችው ዲጂታል መታወቂያ ውጤታማ ሆናለች ብለዋል።


በኢትዮጵያ የተመዘገቡትን አይነት የተሻሉ አፈጻጸሞች ለሌሎች ሀገራት መነሳሳትን የሚፈጥሩና ልምድ የሚወሰድባቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሂ(ዶ/ር) በበኩላቸው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለዲጂታላይዜሽን በተሰጠው ትኩረት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።


በዲጂታል መታወቂያና በፓስፖርት ላይ የማጭበርበር ተግባራት እንዳይፈፀሙ ጠንካራና አስተማማኝ ሲስተም መዘርጋቱን አስታውቀዋል።

ለዚህ ደግሞ የዲጂታል ጉዞውን የሚያፋጥኑ የህግ ማዕቀፎች፣ የመሰረተ ልማትና የሰው ሃይል ግንባታዎች አስቻይ ሁኔታ መፍጠራቸውን በማንሳት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.