አዲስ አበባ፤ግንቦት 16/2017 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የተገነቡ የልማት ስራዎች የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ይበልጥ እንዲወጡ የሚያነሳሱ ናቸው ሲሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተከናወኑ የልማት ስራዎችን የጎበኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ ባለፉት የለውጥ አመታት አካታች የንግድ ስርዓትና ዘመናዊ የገቢ አሰባሰብ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውም ገልጿል።
ከአዲስ አበባ የተለያዩ አካባዎች የተወጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል፣ አቃቂ የእንስሳት ልህቀት ማእከል፣ ለሚ ኩራ ወተር ፓርክ እና የገላን ጉራ መኖርያና የተቀናጀ የልማት መንደርን ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እንደገለጹት፤ በከተማዋ የተገነቡ የልማት ስራዎች የከተማዋን ፈጣን እድገት በተግባር የሚያሳዩ ናቸው።
የሾላ ገበያ ነጋዴ ቴዎድሮስ ተሾመ በሰጡት አስተያየት፥ የልማት ስራዎቹ ወጥነት ባለው መንገድ የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው በአጭር ጊዜ የተገነቡ መሆናቸው ይበልጥ ሳቢና ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል ተስፋዬ ገብረኪዳል በበኩላቸው፥የንግዱ ማህበረሰብ ግብሩን በወቅቱና በአግባቡ በመክፈል የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ይበልጥ እንዲያጠናክር የልማት ስራዎቹ በእጅጉ የሚያነሳሱ ናቸው ብለዋል።
የኮንስትራክሽን ግብዓት ነጋዴ ጀበል ጀማል የትኛውም ልማት በመንግስት ብቻ መከናወን እንደማይችል ጠቁመው፤ ከህዝብ የሚሰበሰብ ግብር ለታለመለት አላማ ውሎ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የሚኒ ማርኬት ዘርፍ ነጋዴ ናትናኤል ቃበታ እንዲሁ በሁሉም መስክ የተሰማራ የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በመወጣት ለአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት መረጋገጥ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍሰሃ ጥበቡ በበኩላቸው፥ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሳምንታት በከተማዋ ከሁሉም ክፍለ ከተማ ከተወጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ባለፉት የለውጥ አመታት በተከናወኑ የልማት ስራዎች ዙሪያ ውይይት ሲያካሒድ ቆይቷል ብለዋል።
ዛሬ የተካሔደው ጉብኝትም የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸው፥የንግዱ ማህበረሰብ የልማቱ ባለቤት መሆኑን ለማስገንዘብ እድል የፈጠረ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በተጨማሪም የንግዱ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ ከመንግስት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር እንዲሁን ተሳትፎውን እንዲያጠናክር የሚያስችል ነውም ብለዋል።
በጉብኝቱ ከሁሉም ክፍለከተማ የተወጣጡና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ከ550 በላይ ጎብኚዎች ተሳትፈዋል።