የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የባቡር መሠረተ ልማቱ ደህንነት ተጠብቆ የተሳካ አገልግሎት እንዲሰጥ ኃላፊነታችንን እንወጣለን

May 26, 2025

IDOPRESS

ድሬደዋ፣ግንቦት 16/2017(ኢዜአ)፦የባቡር መሠረተ ልማቱን ደህንነት በመጠበቅ የተሳካ አገልግሎት እንዲሰጥ ተቀናጅተው እንደሚሰሩ የሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን እና የድሬደዋ አስተዳደር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር የባቡር ደህንነትን ለመጠበቅ የሚያስችል ውይይት ከሲቲ ዞንና ከድሬደዋ አስተዳደር የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ኡጋዞች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የባቡር መሠረተ ልማትና ደህንነት በመጠበቅ የተሳካ አገልግሎት እንዲሰጥ ተቀናጀተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የሶማሌ ኢሳ ማህበረሰብ ኡጋዝ ተወካይ አቶ አብዶ ኡመር ለኢዜአ እንደገለፁት፥ ባቡር የአገራችን የወጭና ገቢ ንግድ ማመላለሻና የብልፅግና ማሳኪያ አውታር ነው።

በተጨማሪም ለሲቲ ዞን ሁለንተናዊ ዕድገትና ለአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ባቡሩ በሚያልፍበት የሲቲ ዞን ከእንስሳትና ከሰው ጋር በተያያዘ የሚገጥሙትን አደጋዎችና የፀጥታ ችግሮች በተደራጀ እና በተቀናጀ መንገድ እንከላከላለን ብለዋል።

አጋዝ አብዱረዛቅ አጋዝ አሊ በበኩላቸው፥ የሚመሩትን የህብረተሰብ ክፍል በማስተባበር የባቡር መሠረተ ልማትና የሚጓዝበትን መስመሮች እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የባቡር መሠረተ ልማት የህልውናችን ጉዳይ በመሆኑ እኛ የአገር ሽማግሌዎች መስመሩን በተቀናጀ መንገድ መጠበቅ ይገባናል ያሉት የድሬደዋ የአገር ሽማግሌና አባገዳ አቶ ጉይሳ ኢብሳ ናቸው።

ለባቡሩ ደህንነት የወጣውን መመሪያ በአግባቡ በመተግበር ባቡሩን ከእንሰሳትና ከሰው ንክኪ መጠበቅ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙና አህመድ በበኩላቸው፥ የባቡር መስመሩ በሚያልፍባቸው ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር የተካሄደው ውይይት የባቡር ትራንስፖርት ደህንነትና ሰላማዊ ጉዞ ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የድሬደዋና የሲቲ ዞን የህብረተሰብ ክፍሎች የባቡርን ጥቅም የሚረዱና በመሆናቸው ባቡሩ በምንም አይነት ሰው ሰራሽ ችግሮች እንዳይስተጓጎል እያደረጉ የሚገኙትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውን የባቡር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብን ህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲረዳ ማሳወቅ መቻሉን ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ኡጋዞች፣የአገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የሲቲ ዞንና የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች እና የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.