የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የታየው መነቃቃት የሀገርን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት የሚያኖር ነው - አህመዲን መሐመድ(ዶ/ር)

May 26, 2025

IDOPRESS

ደብረ ብርሃን፤ ግንቦት 17/2017(ኢዜአ)፦ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የታየው መነቃቃት የሀገርን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት የሚያኖር መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አህመዲን መሐመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

በክልል ደረጃ "ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሃሳብ የንቅናቄ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።


በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አህመዲን መሐመድ(ዶ/ር)፤ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በሁሉም ዘርፎች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተው በተለይም በአምራች ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት እየተፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ሌሎችም ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት ለኢንዱስትሪው እድገት ወሳኝ መሆኑን አንስተው የዘርፉ መነቃቃት ከውጭ የሚገባውን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እያስቻለ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በኬሚካል፣ በብረታብረት፣ በመድሃኒትና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች እድገትና ብልጽግና ለማምጣት እንደሀገር የተያዘውን ግብ ለማሳካት ቅንጅታዊ ስራዎች እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ለዚህም በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ድጋፍ እንደሚደረግና ለአዳዲስ ኢንቨስተሮች የሚደረጉ ማበረታቻዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የታየው መነቃቃት የሀገርን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት የሚያኖር መሆኑን ተናግረዋል።


የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ እንዲሪስ አብዱ፤ በክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፉ አበረታች ውጤት እንዲያመጣ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ብቻ በክልሉ 288 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄ አቅርበው እየተስተናገዱ መሆኑን አንስተዋል።


የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት፤ በበኩላቸው በከተማዋ በተለይም ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረትና እየተመዘገበ ያለው ውጤት ጥሩ የሚባል መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት እስካሁን 25 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ስራ ጀምረው ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በለፉት 10 ወራት 151 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.