አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2017(ኢዜአ)፦ በ10 የፌደራል ተቋማት፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የተገነቡ ስማርት የኮሙኒኬሽን ማሳለጫ ክፍሎች ተመርቀው በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
የስማርት ኮሙኒኬሽን ማሳለጫ ክፍሎቹ የተለያዩ ቦታ ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላትን በቀላሉ እንዲገናኙና ስራቸውን እንዲያሳልጡ የሚያስችሉ ናቸው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በዛሬው እለት ስራ የጀመሩት ስማርት የኮሙኒኬሽን ማሳለጫ ክፍሎች ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ የተሟላላቸውና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ የተገነቡ ናቸው ብለዋል።
ማዕከላቱ የተፋጠነና የተማከለ የስራ ግንኙነት እንደሚፈጥሩ በማንሳት፥ በአግባቡ መጠቀምና ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶ/ር) ስማርት የኮሙኒኬሽን ማሳለጫ ክፍሎቹ ለመረጃ ልውውጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም እነዚህን ማዕከላት በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ በመግለጽ።
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች እየለሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ(ዶ/ር) ናቸው።
ስማርት የኮሙኒኬሽን ማሳለጫ ክፍሎቹ ልዩ ልዩ ስራዎችን፣ ስብሰባዎችንና ስልጠናዎችን ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በቀላሉ መምራት የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ተዘርግተውላቸዋል።
ስማርት ስክሪን፣ ስማርት ላይቲንግ፣ የተሻሻሉ የቴሌ እና የቪዲዮ ኮንፍረንሶችን ማድረግ የሚያስችሉ የኔትወርክ፣ የድምፅ ብክለትን የሚቀንሱ(Soundproofing) መሳሪያዎች ተገጥሞላቸዋል።