አርባ ምንጭ፤ግንቦት 21/2017 (ኢዜአ)፦የአርባ ምንጭ ከተማ የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች ምቹ የመዝናኛ ሥፍራ ከመፍጠር ባለፈ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢዜአ ካነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ሃይሉ ሀብታሙ፥ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ በርካታ ወጣቶች በልማቱ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል።
የከተማውን መሰረተ ልማት በማሳደግ፣ገጽታዋን በመቀየርና የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና የነዋሪውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማሳደጉንም ገልጿል።
በከተማዋ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የመዝናኛ ሥፍራዎች የእረፍት ጊዜን በአልባሌ ስፍራ ከማሳለፍ እንደሚታደጉና በሥራ የደከመ አዕምሮን እንደሚያድሱ የገለጹት ደግሞ አቶ ተሾመ ተገኝ ናቸው።
ሌላዋ የእዚሁ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ወሰኔ ታደሰ በኮሪደር ልማት የሚገነባ መንገድ የእግረኛና ተሽከርካሪ መንገድን ማካተቱ የአደጋ ሥጋትን እንደሚቀንስ ገልጸው፥ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማሳለጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
በከተማው የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለህብረተሰቡ አማራጭ የመዝናኛ ስፍራ ከመፍጠር ባለፈ በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በመንገድ ግራና ቀኝ ደረጃውን የጠበቀ መብራት መኖር በምሽት ያለ ምንም ስጋት ለመንቀሳቀስና ጸጥታን በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ ያስችላል ብለዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዳሙ ሻምቤል በበኩላቸው እንዳሉት፣ በከተማዋ በ2 ቢሊዮን ብር የ10 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተጠናቀቀ ይገኛል።
በኮሪደር ልማቱ ከ600 ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
በኮሪደር ልማት የእግረኛ፣የሳይክልና የተሽከርካሪ መንገድ እንዲሁም መዝናኛ ስፍራዎች መካተታቸውን ገልጸው፥ልማቱ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማፋጠን ባለፈ የኢኮ-ቱሪዝምን ያሳድገዋል ብለዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ በአንደኛ ዙር የኮሪደር ልማት በ500 ሚሊዮን ብር ወጪ 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የግንባታ ሥራ መከናወኑ ይታወሳል።