ሆሳዕና፤ ግንቦት 21/2017(ኢዜአ)፦ የስራ ፈጠራ አማራጮችን ወደ ውጤት መቀየር የሚያስችሉ አሰራሮችን በመተግበር ስራ አጥነትን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ እና በኦሞ ባንክ የተዘጋጀ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ብድር ስርጭትና አመላለስ ላይ ያተኮረ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡
በሚኒስቴሩ የስራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ በመርሃ ግብሩ ላይ የስራ ፈጠራ አማራጮችን ወደ ውጤት መቀየር የሚያስችሉ አሰራሮችን በመተግበር ስራ አጥነትን ለመቅረፍ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለተግባራዊነቱም የክህሎት፣ የስልጠናና የገበያ ትስስር ድጋፍ መደረጉንና ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶችን ለማጠናከርም የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ፖሊሲ መቀረጹን አስረድተዋል፡፡
በተለያየ የስራ መስክ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን ሽግግር ለማስፋት የብድር አቅርቦትና ስርጭት፣ የዕርስ በርስ ልምድ ልውውጥና ምርቶችን የማስተዋወቅ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና የመንግሥት ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ የዜጎችን የስራ አጥነት ችግር በመቅረፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ጸጋዎችን ወደ ልማት ለመቀየር ድጋፍና ክትትል እንዲሁም የመነሻ ካፒታል የማቅረብ ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ ሙስጠፋ ሀሰን በክልሉ የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ በአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችን ለይቶ መጠቀም የሚያስችል ዕቅድ በማዘጋጀት ዘላቂና አስተማማኝ የስራ ዕድልን ለመፍጠር ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የስራ ሀሳብን ወደ ሀብት መቀየር እንዲቻል በተደረገው ጥረት በርካታ ኢንተርፕራይዞች ከጥቃቅን ተቋምነት ተነስተው ወደ ኢንደስትሪ ደረጃ ማደግ መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡
የኦሞ ባንክ ፕሬዚዳንት አብርሃም አላሮ በበኩላቸው ባንኩ የተለያዩ የብድር አማራጮችን በማቅረብ የዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት ያጠናክራል ብለዋል፡፡