የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት በህጋዊ መንገድ የሚላከውን ሬሚታንስ እንዲሻሻል አድርጓል-የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት

Jun 3, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ግንቦት 24/2017(ኢዜአ)፦በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መተግበር የጀመረው ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት በህጋዊ መንገድ የሚላከውን ሬሚታንስ እንዲሻሻል ማድረጉን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።


በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ሬሚታንስ ወደ ሀገር ውስጥ መላኩም ተገልጿል።


የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መንግስት በተለያየ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያፈሩትን ሃብትና እውቀት በሀገራቸው ኢንቨስት በማድረግ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ሲያመቻች ቆይቷል።


በተደረጉ የምጣኔ ሃብት ማሻሻያዎችም የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት እና ሬሚታንስን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።


እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት መተግበሩ በባንኮችና በትይዩ ገበያው መካከል ያለውን የምንዛሬ ልዩነት በማጥበብ በህጋዊ መንገድ የሚላከውን ገንዘብ እንዲጨምር አድርጓል።


ለአብነትም በ2016 ዓ.ም አጠቃላይ የተላከው ሬሚታንስ 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑን በማውሳት፥ በ2017 ዓም ዘጠኝ ወራት ብቻ 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ ኢትዮጵያ መላኩን ተናግረዋል።


ለኢንቨስትመንት የተዘረጉ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ዳያስፖራው በሀገሩ ላይ በኢንቨስትመንት ተሰማርቶ ተጠቃሚ እንዲሆን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።


በዚህም በግላቸው እንዲሁም ለውጭ ባለሃብቶች በተፈቀዱ ዘርፎች ላይ ደግሞ በጥምረት ለመስራት በሂደት ላይ የሚገኙ ዳያስፖራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።


የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ መከፈት ዳያስፖራው በአካል መገኘት ሳያስፈልገው ካለበት ሆኖ በዲጂታል መንገድ አክሲዮን በመግዛትና በመሸጥ ኢንቨስት ማድረግ የሚችልበት እድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።


ዳያስፖራው በኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በእውቀት ሽግግር፣ በአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ አምባሳደር ፍጹም ተናግረዋል።


ዲያስፖራው አገራዊ በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፈ ሲሆን፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ “የመጨረሻ አሻራውን ያኑሩ” በሚል መሪ ሀሳብ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።


በአውሮፓ የዲፌንድ ኢትዮጵያ ዐቢይ ኮሚቴ አባልና በጣሊያን የሚኖሩት ኪያ ነጋሽ በሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።


በታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችና ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፥ ቀጣይም የባህር በር ጉዳይን ጨምሮ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።


የኖርዌይ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሳሁን ገድሉ በበኩላቸው፥ የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የሀገርን ልማት የሚያፋጥኑ ፕሮጀክቶችና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ስራዎቸ ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።


መንግስት ያደረገውን የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ ተከትሎ በዳያስፖራው ዘንድ በህጋዊ መንገድ ገንዘብ ወደ ሀገር ቤት የመላክ ፍላጎት መጨመሩን ተናግረዋል።


ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መንግስት እየወሰዳቸው የሚገኙ ማሻሻያዎች የሚበረታታቱ መሆናቸውን በማንሳት፥ ኢንቨስት ለማድረግ በሂደት ላይ እንደሆኑም አስረድተዋል።


በሀገር ውስጥ እየተደረገ ያለውን የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ በመጠቀም ሬሚታንስን በህጋዊ መንገድ በመላክ፣ በኢንቨስትመንት በመሳተፍ፣ ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ በመቆም ለሀገር እድገት መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.