መቱ፤ ግንቦት 24/2017(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል እየተገነቡ ከሚገኙ 51 የአነስተኛና መለስተኛ የመስኖ ግድቦች መካከል 17ቱ በዓመቱ መጨረሻ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ የክልሉ የመስኖና አርብቶ አደሮች ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ በኢሉአባቦር ዞን ዳሪሙ ወረዳ እየተገነባ የሚገኘውን የሆማ ሆቢ ፊና ፕሮጀክት ግንባታ ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል።
የክልሉ መንግስት 'ፊና ፕሮጀክት' በተሰኘ መርሃ-ግብር በክልሉ ቆላማ እና የአርብቶ አደር አካባቢዎች አነስተኛና መለስተኛ የመስኖ ግድቦችን ገንብቶ የማህበረሰቡን የውኃ ችግር ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በክልሉ የተለያዩ ዞኖች 51 አነስተኛ እና መለስተኛ የመስኖ ግድቦች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
በግንባታ ላይ ከሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 17ቱ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ገልጸዋል።
የክልሉ መስኖና አርብቶ አደሮች ቢሮም ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
በኢሉአባቦር ዞን ዳሪሙ ወረዳ በ175 ሚሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የሆማ ሆቢ ፊና ፕሮጀክት ግንባታው ከተጀመረ ሁለት ዓመታትን ማስቆጠሩን ጠቅሰዋል።
ግንባታው ገና 37 በመቶ ላይ በመሆኑ በአስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲጠናቀቅ የሚያስችል ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በኢሉአባቦር ዞን በአጠቃላይ ከ2 ሺህ 200 ሔክታር በላይ መሬት ማልማት የሚያስችሉ አነስተኛና መለስተኛ የመስኖ ግድቦች እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሐመድጠሃ አባፊጣ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተሰራ በሚገኘው ስራ ተጨማሪ ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።