አሶሳ፤ግንቦት 24/2017(ኢዜአ):- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ የግል ባለሃብቶች እያደረጉት ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
በአሶሳ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የፌዴራል፣የክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት አስፈጻሚዎች የጋራ የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ከውይይቱ በተጓዳኝ በክልሉ በባለሃብቶች እየለሙ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ከተጎበኙት የኢንቨስትመንት ስራዎች መካከል በሆሞሻ ወረዳ የሚገኘው ፍቃዱ ነመራ የተቀናጀ የእርሻ ልማት ድርጅት እና በአሶሳ ከተማ የሚገኘው የእምነበረድ ፋብሪካ ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዝናቡ ይርጋ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት፥ባለሃብቶች የክልሉን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሠማራታቸው ለክልሉ የኢኮኖሚ አቅም መጠናከር ያግዛል።
ክልሉ በሁሉም አማራጮች ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፥በቀጣይም ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም የክልሉን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የኢንቨስትመንት ስራዎች በሁሉም አካባቢ ሊስፋፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ባለሃብቶች የማስተዋወቅ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የሶማሌ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዘይነብ ሐጂአደን እና የጋምቤላ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተወካይ ኡፒየው ኡነክ እንደተናገሩት፥ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው የተፈጥሮ ሀብት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ያግዛል።
በተለይም ክልሉ ለግል ባለሃብቶች የፈጠረው ምቹ ሁኔታ እንደ ተሞክሮ የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመው፥ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በዘርፉ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ አይተናል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በነበራቸው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የምክክር መድረክም በዘርፉ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን በማረም እና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
በጉብኝቱ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች፣ የፌዴራል፣የክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ አመራሮች ተገኝተዋል።