የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ለአርሶ አደሩ መሰጠቱ ምርታማነትና ገቢ ይበልጥ እንዲያድግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

Jun 3, 2025

IDOPRESS

ባህርዳር፤ ግንቦት 25/2017 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ለአርሶ አደሩ መሰጠቱ ከወሰን ጋር ተያይዞ ያጋጥም የነበረውን ችግር በማስቀረት ምርታማነትና ገቢ ይበልጥ እንዲያድግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጸ።

በክልሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች እንዳመለከቱት፤ ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታቸው በመሬታቸው ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

በበጀት ዓመቱ እስካሁን ለ382 ሺህ ባለይዞታዎች ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠቱን የክልሉ መሬት ቢሮ አስታውቋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን የሞረትና ጅሩ ወረዳ አርሶ አደር ዱባለ ስንታየሁ ፤ ባላቸው መሬት ልክ በካርታ የተደገፈ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም የመሬታቸውን ካርታ በዋስትና በማስያዝ በወሰዱት ብድር አይሱዙ የጭነት መኪና በመግዛትና ወደ ስራ በማስገባት የተሻለ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል።

ይህም በራሳቸው ከሚያከናውኑት የግብርና ልማት በተጨማሪ እንደሆነ አመልክተው፤ ትምህርታቸውን ላጠናቀቁ ልጆቻቸው በሹፍርናና ሌሎች ስራዎች የስራ ዕድል ማመቻቸታቸውን አስረድተዋል።

የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ቅጣው ለማ በበኩላቸው፤ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታችን ከወሰን መጋፋት ጋር ተያይዞ ያጋጥም ከነበረ መጨቃጨቅ በመላቀቅ መሬታቸው ለምነቱ ተጠብቆ ምርታማነቱን እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም የመሬታቸውን ካርታ በዋስትና አስይዘው ገንዘብ በመበደር ባመቻቸቱ ተጨማሪ ስራ የተሻለ ገቢ እያገኙ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ እንደረዳቸው አመልክተዋል።

በይዞታ መሬታቸው ካርታ ከፀደይ ባንክ 100 ሺህ ብር በመበደር ተጨማሪ መሬት ተከራይተው በማልማት ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ የገለጹት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ አርሶ አደር አማረ አይቸው ናቸው።

ካርታ ማግኘታቸው ከነበረባቸው ስጋት ተላቀው መሬታቸውን በመንከባከብ ምርታማነቱ እንዲጨምር የሚያስችል ስራ ሌት ተቀን እንዲሰሩ ያተጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ መሬት ቢሮ የገጠር መሬት አስተዳደርና ካዳስተር ዳይሬክተር አቶ ታከለ ሃብቴ፤ በበጀት ዓመቱ ለ426 ሺህ ባለይዞታዎች ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ለመስጠት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፤

እስካሁን በተደረገ ጥረትም አንድ ሚሊዮን 86ሺህ የእርሻ ማሳዎችን በካዳስተር በመለካት ከ382 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ባለይዞታዎች ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠት ተችሏል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳመለከቱት፤ካርታውን በዋስትና በማስያዝም ከአበዳሪ ተቋማት የገንዘብ ብድር በማግኘት ገቢያቸውን በሚያሳድጉ የተለያዩ የስራ ዘርፎች በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እየጎለበተ ነው።

የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠቱ ከወሰን ጋር ተያይዞ ያጋጥም የነበረውን ችግር በማስቀረት አርሶ አደሩ ሙሉ ጊዜውን ለልማት ስራው በማዋል ምርታማነትን እንዲያሳድግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

በአማራ ክልል በአጠቃላይ 15 ነጥብ 4 ሚሊዮን ማሳ ተለክቶ ቋሚ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር የተሰጠ ሲሆን ፤ ከዚህ ውስጥ ከ13 ሚሊዮን በላይ ማሳ ወደ ዲጅታል ሲስተም መግባቱን ከመሬት ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.