ደብረማርቆስ፤ግንቦት 30/2017(ኢዜአ)፡-በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2017/2018 የምርት ዘመን ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በኩታ ገጠም አሰራር የተጠናከረ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
ምርትና ምርታማነት እያሳደገላቸው ያለውን የኩታ ገጠም አሰራርን አጠናክረው መቀጠላቸውን በዞኑ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ እንቢያለ አለኸኝ እንደገለጹት፥በምርት ዘመኑ የኩታ ገጠም አሰራርን በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም በ2017/2018 የምርት ዘመን 435 ሺህ ሄክታር መሬትን በኩታ ገጠም ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
ይህም በምርት ዘመኑ አጠቃላይ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው ከ640 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም ከ40 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከ31ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ቀድመው በሚዘራ የማሽላና የበቆሎ ሰብል በኩታ ገጠም መሸፈኑን አስታውቀዋል።
በኩታ ገጠም እየለማ ካለው የሰብል ዓይነት መካከል ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ በቆሎና የቢራ ገብስ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።
በኩታ ገጠም ከሚሸፈነው መሬት ላይም ከ18 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመው፥ለስኬቱም ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በዞኑ የጎዛመን ወረዳ የገራሞ ቀበሌ አርሶ አደር ታከለ አቦዝን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፈው ዓመት ከአንድ ሄክታር በላይ መሬታቸውን በኩታ ገጠም ስንዴን በመዝራት በጋራ በማረም፣ ተባይ በመቆጣጠርና ግብአት በመጠቀም ውጤታማ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
ይህም ከዚህ በፊት ያገኙት ከነበረው እስከ ስድስት ኩንታል ጭማሪ እንዳለው ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት ተሞክሮውን በማስፋት በኩታ ገጠም አሰራር ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን ላይ በቆሎ መዝራታቸውን ገልጸዋል።
የኩታ ገጠም አሰራርን ከጀመሩ ባለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ከሚያለሙት ሰብል በፊት ያገኙት ከነበረው ከአራት ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ምርት በማግኘት ተጠቃሚ እንደሆኑ የተናገሩት በደጀን ወረዳ የኩራር ቀበሌ አርሶ አደር ወርቁ ደስታ ናቸው።
ዘንድሮ ደግሞ ከአንድ ሄክታር በላይ ማሳታቸውን በኩታ ገጠም ማሽላ መዝራታቸውን ጠቁመው፤ የባለሙያ ምክረ ሃሳቦችንና ቅንጅታዊ አሰራርን በመተግበር ጭምር ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ እየተጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን በምርት ዘመኑ በአጠቃላይ ለማልማት ከታቀደው መሬት ላይ ከ25 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።