የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በዞኑ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት በትኩረት እየተከናወነ ነው

Jun 9, 2025

IDOPRESS

አምቦ፤ግንቦት 30/2017(ኢዜአ)፦በምዕራብ ሸዋ ዞን ለበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ትኩረት በመስጠት የአቅርቦት እጥረትን ለማቃለል የሚያስችል ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።


በምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ገላን ወረዳ የበቆሎ ምርጥ ዘር ምርት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄዷል።


የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተረፈ አራርሳ እንደገለጹት፥በዞኑ በዘንድሮው የመኸር እርሻ አጠቃላይ ከ886 ሺህ 794 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ይለማል።


እስካሁን በተከናወነ እንቅስቃሴም 280 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።


ከዚህም ውስጥ በመኸር እርሻ በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ምርጥ ዘሮች በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ በክላስተር የማባዛት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከዚህ ውስጥ 500 ሄክታር መሬት የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።


በዞኑ በቆሎን በብዛት ከሚያመርቱት ወረዳዎች አንዱ በሆነው ኢሉ ገላን ወረዳም በ360 ሄክታር መሬት ላይ የበቆሎ ምርጥ ዘር የማባዛት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።


በ2017/18 የምርት ዘመን 300 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን የተናገሩት ደግሞ የአምቦ ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩንየን ኃላፊ አቶ ወንዱ ደጀኔ ናቸው።


ለመኸር አዝመራው 600 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለዞኑ አርሶ አደሮች እንደሚቀርብ ገልጸው ሌሎች የግብርና ግብዓቶች እየቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።


ዩንየኑ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ከማዳበሪያ በተጨማሪ ለአርሶ አደሮች የበቆሎ ምርጥ ዘር እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


በዞኑ የኢሉ ገላን ወረዳ አርሶ አደር ጉርሜሳ ዋቅጋሪ እንደተናገሩት ለስድስት ዓመት በበቆሎ ክላስተር ልማት ላይ እንደተሰማሩ ጠቁመዋል።


በዚህ ዓመትም የበቆሎ ምርጥ ዘር መዝራት መጀመራቸውን ገልፀው ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ እንደሚገኙም ገልፀዋል።


ሌላኛው አርሶ አደር አቶ አዱኛ ጋዲሳ በበኩላቸው፤ በቆሎን ቀደም ብለው እያመረቱ መሆኑን ገልጸው ዘንድሮም የተሻለ ምርት ለማግኘት እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.