የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በሀገራዊ ለውጡ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የላቀ አቅም ተፈጥሯል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

Jun 10, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2017(ኢዜአ)፦ ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት መንግሥት ያካሄዳቸው ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎች የዘላቂ ልማት ግቦችን በመተግበር የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ ትልቅ አቅም መፍጠራቸውን የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

3ኛው ሀገር አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች የፈቃደኝነት ግምገማ ሪፖርት ላይ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ታድመዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.አ.አ 2015 ያጸደቀው የዘላቂ ልማት አጀንዳ 2030 የማይነጣጠሉና ሁሉን አቀፍ የሆኑ 17 ግቦችን ያካተተ ነው።


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በምክክር መድረኩ ባደረጉት ንግግር የዘላቂ ልማት አጀንዳው ድህነትን በማስወገድ የሰው ልጆችን የተሟላ ኑሮና ብልፅግና ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት አጀንዳውን በባለቤትነት እየተገበረች እንደምትገኝም ገልጸዋል።

ከለውጡ ማግስት ሁለንተናዊና አካታች ብልጽግናን ለማረጋገጥ በርካታ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የመልካም አስተዳደር ሪፎርሞች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።

የሪፎርም ስራዎቹ የዘላቂ ልማት ግቦችን በመተግበር ስኬት ለማስመዝገብ የበለጠ አቅም መፍጠራቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የፈቃደኝነት ግምገማ አሠራርን መሠረት በማድረግ ሁሉንም የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም ያካተተ ሪፖርት በማዘጋጀት ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ልምዷን ለሌሎች ሀገራት ማካፈሏን አንስተዋል።


በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት 3ኛውን የፈቃደኝነት ብሔራዊ ግምገማ ሪፖርቷንና ልምዷን ለማቅረብ መዘጋጀቷንም አስታውቀዋል።

ሪፖርቱ ሀገሪቱ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ የልማት ስራዎችን በማከናወን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በአካባቢ ጥበቃ ውጤት እያስመዘገበች እንደምትገኝ ለዓለም የምታሳይበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ዝርዝር ሪፖርቱ ጤናማ ህይወትን፣ የጾታ እኩልነትን፣ አካታችና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ፣ ምቹ ስራን ለሁሉም ማስፋፋት፣ የውሃ ስነ-ምህዳርን ለዘላቂ ልማት መጠበቅ፣ ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ማጠናከርና ሌሎችም የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸምን ያማከለ ነው ብለዋል።


የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ከሀገራዊ የልማት ዕቅዶቿ ጋር በማስተሳሰር በከፍተኛ ኃላፊነት እየተገበረች እንደሆነ ገልጸዋል።

ግቦቹን ለማሳካት ሀገራዊ የልማት ኢኒሼቲቮች ተቀርፀው እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የትምህርት ለትውልድ፣ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የልማት ተግባራት በሁሉም አካባቢዎች በስኬት እየተተገበሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎቹ ድህነትን ለማስወገድ፣ ዘላቂና አካታች የኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ፣ ጤናማ ትውልድ ለመገንባትና ምቹ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጉዞ እያፋጠኑ ነው ብለዋል።

3ኛው ሀገር አቀፍ የዘላቂ ልማት ግብ የፈቃደኝነት ግምገማ ሪፖርትም ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፋዊ ግቦች መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት የምታሳይበት መሆኑን ተናግረዋል።


ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግብን ለማሳካት ያከናወነቻቸው ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን መገንዘባቸውን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ተጠሪና የሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ ራሚዝ አልካባሮቭ(ዶ/ር) ናቸው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.