አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦ የፌዴራል መንግስት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተሳካ ሁኔታ ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና እንዳለው የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 35ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የፌደራል መንግስት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
በማብራሪያቸውም የ2018 በጀት ዓመት የመንግስት ገቢ የውጪ እርዳታን ጨምሮ 1ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር እንደሚሆን ይገመታል ብለዋል፡፡
ይህም በ2017 በጀት ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ ከተገመተው ጠቅላላ ገቢ አንጻር የ62 በመቶ ዕድገት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
ከታክስ ምንጭ የተያዘውን የገቢ ዕቅድም ለማሳካት በታክስ ፖሊሲ እና በታክስ አስተዳደር በኩል የተያዙትን ማሻሻያዎች በተቀናጀ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ከቀረበው የፌደራል መንግስት ረቂቅ በጀት ውስጥ 61 በመቶው ለመደበኛ በጀት የተመደበ መሆኑን አንስተው፣ ይህም በተያዘው በጀት ዓመት ለመደበኛ በጀት ከተመደበው በጀት የ48 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ለፌደራል መንግስት ለካፒታል በጀት የተደለደለው 415 ቢሊዮን ብር ከጠቅላላ በጀት የ22 በመቶ ድርሻ ያለው መሆኑን ተናግረው፤ ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ72 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያለው መሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ለ2018 በጀት ዓመት የተያዘው የፌደራል መንግስት በጀት ከበጀት ዓመቱ ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ጭማሪውም በአብዛኛው ማሻሻያው ተግባራዊ ከማድረግ ጋር የተያያዙ ወጪዎች ጭማሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጀቱ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያ በተሳካ ሁኔታ ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ባለበጀት መስሪያ ቤቶችም የተበጀተላቸውን በጀት ለታለመለት ዓላማ ብሎም በቁጠባና በውጤታማነት ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የሚጸድቀውን በጀት የመንግስትን የፋይናንስ የግዢና የንብረት አስተዳደር ህጎችንና ስርዓቶችን ተከትለው ስራ ላይ በማዋል ወጪ ቁጠባ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በጀቱ በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡