አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2017(ኢዜአ)፦ በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የገጠር ፋይናንስ ማስተባበሪያ መቋቋሙን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶ እና አርብቶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትና የፋይናስ አቅርቦት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) የግብርና እና ገጠር ልማት አጀንዳ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በአነስተኛ ማሳ ላይ እንደሚያመርቱ ገልጸው፣ ሀገሪቱ በጀመረቻቸው ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለገጠር ልማትና ግብርና ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቷን አንስተዋል።
የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የግብርና ግብዓቶቸን በማሟላትና የብድር አቅርቦትን በማሳደግ በኩልም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።
የመሬት አጠቃቀም አዋጅ መጽደቅ እንዲሁም የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ መደረግ በአነስተኛ ማሳ የሚያመርቱ አርሶ እና አርብቶ አደሮችን በፋይናንስ ዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በየዓመቱ የምትተክላቸው ችግኞች የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ በምግብ ራስን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት እያገዘ ነው ብለዋል።
አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ እና አርብቶ አደሮች የፋይናንስና የኢንሹራንስ ተጠቃሚ በማድረግ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ለዚህም የገጠር ፋይናንስ ማስተባበሪያ ዩኒት መቋቋሙን ነው ያነሱት።
የገጠር ፋይናንስ ማስተባበሪያው ለአርሶ አደሮች የብድር አቅርቦት ተደራሽነትን ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
የግብርና አደጋ ስጋትን የሚቀንስ የኢንሹራንስ አገልግሎትን በማሳደግ አርሶ አደሩ በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርስበትን ጉዳት መቀነስ እንደሚያስችልም አንስተዋል።
የማስተባበሪያ ማዕከሉም የአርሶ አደሮችን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት እንደሚያጠናክር ገልጸው፥ ለዘላቂና ስኬታማ ስራ የባለድርሻ አካላት ትብብርና ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ ነው ብለዋል።
የጌትስ ፋውንዴሽን ከፍተኛ ፕሮግራም ኦፊሰር ሳሚ ሲምቤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግብርናው ዘርፍ አስድናቂ ለውጦችን እያሳየች መሆኑን አንስተዋል።
የተገኙ ስኬቶችን ለማጠናከር አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮችን የአደጋ ተጋላጭነት በተቀናጀ መልኩ መቀነስ ይገባል ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በአነስተኛ ማሳ በሚያመርቱ አርሶ አደሮች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስም የኢንሹራንስ አገልግሎትን ማስፋት፣ ተቋማትን ማጠናከርና ፖሊሲዎችን ማጎልበት ይገባል ነው ያሉት።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ(ዶ/ር) በበኩላቸው የግብርና ዘርፉ የስራ ዕድል በመፍጠርና የወጪ ንግዱን በማሳደግ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ዋነኛ ሞተር መሆኑን አንስተዋል።
ይህን ለማጠናከርም ለባለ አነስተኛ ማሳ አርሶ እና አርብቶ አደሮች የተቀናጀ የፋይናንስና የኢንሹራንስ አቅርቦትን ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መድህን ሰጪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ያሬድ ሞላ፥ የተቀናጀ የኢንሹራንስ አገልግሎትን መተግበር ለአርሶ አደሮች እፎይታ በመስጠት የግብርና ስራን ውጤታማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።