አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከእንስሳት ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር ማድረጉን የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢኒስቲትዩት ገለጸ።
በ2017 በጀት ዓመት 10 ወራት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ኢኒስቲትዩቱ አስታውቋል።
የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስራት ጤራ ለኢዜአ፤ በ2017 በጀት ዓመት ከሥጋ፣ ከዕርድ ተረፈ ምርት፣ ከማር፣ ከሰምና ሰም ውጤቶች፣ ከወተትና ወተት ተዋጽኦዎች 122 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅ ዶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ውስጥ 100 ነጥብ 23 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸው ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ28 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
እንደ ዶክተር አስራት ገለጻ 98 በመቶ የሚሆነው ገቢ የተገኘው ከበግ፣ ፍየል፣ ዳልጋ ከብቶችና የግመል ሥጋ ቀሪው ገቢ ከማር፣ ከግመል ወተትና ከዶሮ ምርቶች ነው።
ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የተዘረጉ አሰራሮች ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተዳምሮ በመስኩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲጨምር ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።
ለአብነትም ባለፈው በጀት ዓመት 10 ወራት የተገኘው ገቢ 63 ነጥብ 2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደነበር አስታውሰው የ2017 በጀት ዓመት 10 ወራት ገቢ ወደ 100 ነጥብ 23 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ማለቱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ለስኬቱ መገኘት መሰረቱ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ይወጡ የነበሩ የእርድ እንስሳቶች ወደ ሕጋዊ ኤክስፖርት ቄራዎች መምጣት መጀመራቸውና በጥቁር ገበያውና በባንኮች መካከል ያለው የውጭ ምንዛሬ ተመን መቀራረብ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዶክተር አስራት እንደገለጹት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር የኢትዮጵያን የእንስሳት ምርቶች በስፋት የሚገዙ ናቸው፡፡
ለቄራዎች የእርድ እንስሳትን በብዛት ለማቅረብ ነጋዴዎችና ህብረት ሥራ ማህበራትን የማስተሳሰር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም አብራርተዋል።
የእርድ እንስሳት አቅርቦትን ለማሳደግ ኤክስፖርት ቄራዎችና አርብቶ አደሮች ውል ፈርመው በጋራ የሚሰሩበት የኮንትራት እርባታ አሰራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
በሙከራ ደረጃም 120 የደቡብ ኦሞ አርብቶ አደሮች ወደ ኮንትራት እርባታ አሰራር እንዲገቡ መደረጉን ገልጸው ከደቡብ ኦሞ የሚገኘውን ተሞክሮ በመቀመር ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋት ሥራ እንደሚከናወንም አመልክተዋል።
የተሻሻለ ዝርያ እና ጤናው የተጠበቀ የእንስሳት እርባታ ሥርዓት በመዘርጋት ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም እንዲያድግ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።