አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2017(ኢዜአ)፦አዲስ አበባ በፈጣን የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የምትጓዝ መንገዶቿ ሰላም የሰፈነባቸው አስደናቂ ከተማ ሆና አግኝተናታል ሲሉ የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ኃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡
በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በምክር ቤቱ ስብሰባ ከዓለም ዙሪያ ካሉ 55 የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን አባል ቤተ ክርስቲያናት ተወካዮች የተሳተፉበት ውጤታማ ኹነት እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጳጳስ ሄነሪክ ስቱብኬር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ ቆይቷል።
የምክር ቤቱን ስብሰባ ዳግም ሲካሄድ ኢትዮጵያ ኹነቱን በጥሩ መንገድ ማስተናገድ እንደምትችል ታምኖባት መመረጧን ጠቁመዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስትና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ አስደናቂ ትብብር በመፍጠር የጉዞ ሰነዶች በቀላሉ ተጠናቀው ተሳታፊዎች ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ እጅግ አስደሳች ጊዜ ማሳለፋቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ተሳታፊዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ውብ አዲስ አበባ መመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል።
የታንዛኒያ ኢቫንጀሊካል ሉተራን ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እና የፌዴሬሽኑ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ፕሬዚዳንት ፍሬድሪክ ሾ በአዲስ አበባ ከተማ ውበት እጅግ በጣም ተደንቄያለሁ ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ተዘዋውሬያለሁ፤ በፈጣን የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ መሆኗን በሚገባ ተመልክቻለሁ ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የተሰሩ ስራዎች የለውጥ ምልክቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ዋና ጸሀፊ ቄስ ዶክተር አኔ በርክሀርድት በኢትዮጵያ ቆይታቸው አስደናቂ አገልግሎት አግኝተናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የዓለም አቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ትልቁ አባል በመሆኑ በኢትዮጵያ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡