አዲስ አበባ፤ ሰኔ 15/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የመዲናዋን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት የሚመጥኑ መሆናቸውን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ገለጹ።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የተወያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት የሃላላ ኬላ ኢኮ-ቱሪዝም ሪዞርት እና የጊቤ-3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ጎብኝተዋል።
በዚሁ ጊዜ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተገነቡ የልማት ስራዎች ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን አንስተዋል።
በተለይም በአዲስ አበባ የተገነቡ እና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ከተማዋ ተጭኗት የነበረውን ጎስቋላ ገጽታ በመቀየር ዓለም አቀፍ ስምና ዝና እንድትጎናጸፍ የሚያስችላት ናቸው ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአጭር ጊዜ በጥራትና በፍጥነት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የመዲናዋን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት የሚመጥኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ሀጂ እስማዔል መሀመድ አዲስ አበባ ከተማ በጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገበችው የልማት ስኬት እንዳስደመማቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የልማት ስራዎች የበኩላቸውን ገንቢ ሚና በመወጣት ለዜጎች የጋራ ተጠቃሚነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የወጣቶች ክንፍ ምክትል ሰብሳቢና የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የወጣቶች ክንፍ ኃላፊና የሥራ አስፈፃሚ አባል ጥጋቡ ደጀኔ በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት በማሳደግ ለሌሎች ከተሞች ዕድገት ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ክልል የኢዜማ ምክትል መሪ ጋትቤል ቦል በበኩላቸው አዲስ አበባን ውብ ገጽታ አንድትላበስ ላስቻሉ መሪዎችና የልማት አጋሮች ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።