አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከአሜሪካው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ኩባንያ ጋር በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመ።
ሥምምነት መርሃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተገኙበት በአንጎላ ሉዋንዳ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ አሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ ጎን ለጎን ነው የተከናወነው።
ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እና የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ኩባንያ ጋሬት ጊሽ ፈርመውታል።
ሥምምነቱን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ተቋም ጋር ከ200 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ካፒታል በኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለመሰማራት የሚያስችለው መሆኑ ተገልጿል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ሥምምነቱ ኢትዮጵያ የምትፈልገውና ከልማት ፕሮግራሟ ጋር አብሮ የሚሄድ ትልቅ የኢንቨስትመንት ሥምምነት መሆኑን አንስተዋል።
ሥምምነቱ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን አዎንታዊ ውጤት ይበልጥ ወደፊት አጠናክሮ ለማስቀጠል ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሥምምነቱ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ አበረታች ውጤት እያስመዘገበች ባለበት ወቅት መፈረሙን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ዛሬ የተደረሰው ሥምምነት በዘርፉ የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች ለማስቀጠል እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ የሚያደርገው ተሳትፎ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ጭምር ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል።
የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ፕሬዝዳንትና ሥራ አስፈጻሚ ጋሬት ጊሽ በበኩላቸው ሥምምነቱ አሜሪካ አፍሪካን በተመለከተ ለማጠናከር ያሰበችውን የንግድና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲ የተከተለ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ ኩባንያው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ተሳትፎው ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ እድገት የበኩሉን አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።