አዲስ አበባ፤ሰኔ 17/2017(ኢዜአ)፦የምስራቅ አፍሪካ መሠረተ ልማት እና የውሃ ኤክስፖ በኢትዮጵያ በግንባታና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ አዳዲስ አሰራሮችን እና ቴክኖሎጂዎች ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ ለ3ኛ ጊዜ ከሰኔ 19 እስከ 21 ቀን 2017 ዓም ድረስ በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄደውን የምስራቅ አፍሪካ መሠረተ ልማት እና የውሃ ኤክስፖን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
ይህም ለአገሪቱ ዕድገት ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ እና ተወዳዳሪነትን በተግባር ማሳየት የቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ኤክስፖው በአገሪቱ እያደገ የመጣውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለመደገፍ በእጅጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ በግንባታና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ አዳዲስ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አንስተዋል።
በኤክስፖው በኮንስትራክሽንና ግንባታ ዘርፍ የተሰማሩና ከ20 አገራት የተወጣጡ ከ180 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ምርቶቻቸውን ይዘው እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።
ይህም በዘርፉ ከአገራት ጋር የሚፈጠረውን የንግድና መሠል የገበያ ትስስር ለማጠናከር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አክለዋል።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚፈጠር የስራ እድል ማስፋትና አካታች ልማትን እውን ማድረግ የኤክስፖው አንዱ ዓላማ መሆኑንም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
ኤክስፖው የአገራትን ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም፣ አስተማማኝ የመሠረተ ልማት ግንባታን ተግባራዊ ለማድረግ፣ የተቀናጀ የከተማ መሠረተ ልማትን ለማረጋገጥ እና በቤት ልማት ዘርፍ አዳዲስና ዘመናዊ አሰራሮችን ለመተግበር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ታምኖበታል።
በተጨማሪም በኮንስትራክሽን ዘርፍ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ስትራቴጂዎችን በተገቢው መልኩ ስራ ላይ ለማዋል አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።