የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የወረዳው አርሶ አደሮች ስንዴን በኩታ ገጠም ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ኑሯቸው እየተሻሻለ መጥቷል

Jun 27, 2025

IDOPRESS

አምቦ ፤ሰኔ 18/2017(ኢዜአ)፦ ስንዴን በኩታ ገጠም ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱን በምዕራብ ሸዋ ዞን የወልመራ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በዞኑ ወልመራ ወረዳ የዘንድሮ መኸር አዝመራ በኩታ ገጠም የሚለማ ስንዴ ዘር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የዞኑ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ተካሄዷል።


በዚሁ ጊዜ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወረዳ አርሶ አደሮች ባለፉት ዓመታት ስንዴን በበጋ መስኖ እና በመኸር አዝመራ በማልማት ተጠቃሚነታቸው እያደገ፤ ኑሯቸውም እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

አርሶ አደር ታምራት ረጋሳ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ሶስት ዓመታት ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በጋራ በመሆን በኩታ ገጠም ስንዴን እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል።

በኩታ ገጠም ልማቱም የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ምርቱ እስኪሰበሰብ ድረስ ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በስንዴ ልማቱም ኑሯቸው እየተሻሻለ፤ ተጠቃሚነታቸውም እያደገ በመምጣቱ በተያዘው መኸርም የተሻለ ምርት ለማግኘት ዘር መዝራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ሌላው አርሶ አደር አጀማ ቀቀባ፤ በተያዘው የመኸር እርሻ የተሻለ ምርት ማግኘት የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በኩታ ገጠም ማልማት ከመጀመራቸው በፊት በሄክታር የሚያገኙት ምርት ያነሰ መሆኑን አስታውሰው በኩታ ገጠም ተደራጅተው ማረስ ከጀመሩ ወዲህ ከአንድ ሄክታር እስከ 50 ኩንታል ስንዴ ምርት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ በጊዜ እንደደረሳቸው ተናግረው ለሰብል እንክብካቤ የሚውል ጸረ አረም ኬሚካልም ለማግኘት በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።


የወልመራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርናና መሬት አስተዳዳር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ተሾመ በበኩላቸው የወረዳው አርሶ አደሮች የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን እየተላመዱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በዘንድሮ መኸር እርሻ በወረዳው 32 ሺህ 750 ሄክታር መሬት በተለያዩ የእህል ዘር ለማልማት የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 18 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ይለማል ብለዋል።

በወረዳው 9 ሺህ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ተደራጅተው ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ቀርቦላቸው አስፈላጊ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በወረዳው ከሚከናውነው የስንዴ ልማትም ከአንድ ሄክታር መሬት 60 ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንና 200 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።


የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ኡማ፤ በመኸር እርሻው 886 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዷል ብለዋል።

በመኸር አዝመራው በቆሎ፣ ማሽላ እና ስንዴ በኩታ ገጠም የሚለሙ ሲሆን በዞኑ 263 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ እንደሚለማ አስታውቀዋል።

በምርት ዘመኑ የተሻለ ምርት ለማግኘት የምርጥ የዘር አቅርቦት፣ የማዳበሪያ እና ሌሎች የግብርና ግብአቶች ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.