ጊምቢ፤ ሰኔ 19/2017 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ወለጋ ዞን በ66 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በሽታን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ምርት መስጠት የሚችሉ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ተከላ በመከናወን ላይ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ቡና ልማትና ጥራት ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም መስፍን እንዳሉት፤ በዞኑ የተሻሻሉና በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞች ተከላ እየተካሄደ ነው።
በዞኑ የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ያረጁ የቡና ተክሎች የተነቀሉበት ቦታን ጨምሮ በ66 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ላይ የቡና ችግኝ ተከላ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
በአካባቢው ዘንድሮ የዝናብ ስርጭት አነስተኛ በመሆኑ ተከላው ዘግይቶ መጀመሩን የተናገሩት አቶ መስፍን ስራው በተጠናከረ መልኩ በመከናወን ላይ ነው ብለዋል።
የቡና ችግኞቹ በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸውና ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም ባለፉት ዓመታት ያረጁ የቡና ዛፎችን በማንሳት በተሻሻሉ ዝርያዎች የመተካት ተግባር በስፋት መከናወኑንም ገልጸዋል።
በዞኑ ከ650 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት የተሸፈነ ሲሆን ዘንድሮ የሚተከሉ የቡና ችግኞች ሽፋኑን ወደ 700 ሺህ ሄክታር መሬት ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል፡፡