የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል በማስተሳሰር ለኢነርጂ ነጠላ ገበያ ትግበራ መሰረት ሆናለች-በአፍሪካ ሕብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽን

Jul 1, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ሰኔ 23/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል በማስተሳሰር ለአፍሪካ አህጉራዊ የኢንርጂ ነጠላ ገበያ ትግበራ መሰረት እየሆነች እንደሚገኝ በአፍሪካ ሕብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽን ገለጸ።

የአፍሪካ ሕብረት ’’የኢነርጂ ነጠላ ገበያ ሁኔታ ግምገማ፣ ተቋማዊ ማሻሻያና የመመሪያ አቀራረብ’’ በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የአፍሪካ ነጠላ የኤሌክትሪክ ገበያ አጀንዳ ከፍተኛ የቴክኒክ ግምገማ ስብሰባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ዳይሬክተር ካሙጊሻ ካዛውራ÷ እ.አ.አ. በ2021 በተካሄደው የሕብረቱ ጠቅላላ ጉባኤ የአፍሪካ የኢነርጂ ነጠላ ገበያ ትግበራ ፍኖታ ካርታ መቀመጡን አስታውሰዋል።

የዘንድሮው ከፍተኛ የቴክኒክ ስብሰባም የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 የኢነርጂ ነጠላ ገበያ የዕቅድ የአፈፃጸም ትግበራ ሂደት ግምገማ የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የመሰረተ ልማትና ኢንርጂ ኮሚሽንም የልማት አጋሮችን በማስተባበር የአህጉሪቷን በኢነርጂ መሰረት ልማት ለማስተሳሰር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአህጉሪቷ አባል ሀገራትም የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ትስስርን በማሳለጥ ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ለሱዳን፣ ጁቡቲና ቀሪ ጎረቤቶቿ ጋር ከፈጠረችው የሃይል ትስስር በተጨማሪም የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት ቀጣናን በኤሌክትሪክ ሀይል እያስተሳሰረች ነው ብለዋል።

ይህም ለአፍሪካ ሕብረት የኢንርጂ ነጠላ ገበያ ትግበራ አቅም እየሆነች መምጣቷን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በአውሮፓ ሕብረት ልዑክ የፖሊሲና የትብብር ክፍል ኃላፊ ጂያንሉካ አዞኒ÷ በአውሮፓ-አፍሪካ የአረንጓዴ ኢነርጂ ልማት ተነሳሽነት መርህ የአህጉሪቷን የሃይል ልማት እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ የኢነርጂ ፋይናንስ መፍትሔዎች፣ የፖሊሲና ደንብ ዳይሬክተር ዋሌ ሾኒባሬ÷ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በታዳሽ የኤልክትሪክ ሃይል ለማስተሳሰር አስደናቂ የልማት ስራ እየሰራች እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክም አህጉሪቷን በኤሌክትሪክ ሃይል በማስተሳሰር ልማቷን አንድታሳልጥ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በጀርመን የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጄ.አይ.ዜድ) የአፍሪካ የኢነርጂ ሽግግር መርሃ ግብር አስተዳደር ሞኒካ ራሜለት÷ አፍሪካ ለዜጎቿ ዕድገት መሰረት የሚሆን ዕቅም የኤሌክትሪክ ሃይል አማራጭ አቅም ያላት አህጉር ነች ብለዋል።

የጀርመን የልማት ትብብር ኤጀንሲም አህጉሪቷ ለዜጎቿ ተመጣጣኝ፣ ዘላቂና አስተማማኝ የሃይል ልማት ለማሳለጥ በምታደርገው ጉዞም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ላይ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት የዘርፉ የስራ ሃላፊዎችና ሙያተኞች እንዲሁም የልማት አጋርና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የስራ ሃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.