የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በዞኑ የቡና ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የአምራቹን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

Jul 3, 2025

IDOPRESS

ነቀምቴ ፤ ሰኔ 25/2017(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ወለጋ ዞን የቡና ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የአምራቹን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጎለብቱ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በጽህፈት ቤቱ የቡና ልማት ቡድን መሪ አቶ አሰፋ መኮንን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

በተለይ የተሻለ ምርት የሚሰጡ ቡና ችግኝ ማፍላት፣ የቡና ችግኝ የሚተከልበት ቦታ የማዘጋጀት፣ ያረጀ ቡናን የመጎንደል ስራዎችን ጠቅሰዋል።


በዚህም በዞኑ ለቡና ችግኝ መትከያ የሚውል 43 ሺህ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ገልፀው፤ በዚሁ መሬት ላይ የሚተከል የቡና ችግኝ በመንግሥት እና የግል ችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች መሰናዳቱን ተናግረዋል።

በቡና ምርት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በቡና ችግኝ ተከላው በመሳተፍ ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ በባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም አንስተዋል።

በተላይ አርሶ አደሮቹ በቡና ምርት ሂደት ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ለማበረታታት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተናግረዋል።

በዞኑ ቡናን በስፋት ከሚያመርቱ ወረዳዎች መከከል ሲቡ ሲሬ ወረዳ አንዱ ሲሆን ፤ በወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የቡና ልማት ሀላፊ አቶ አዳነ አሸናፊ፣ የወረዳው አርሶ አደሮች ቡናን በኩታ ገጠም በማልማት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በወረዳው በተያዘው ክረምት የተሻለ ምርት የሚሰጥ የቡና ችግኝ በመደበኛ እና በኩታ ገጠም በተዘጋጀ መሬት ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

የሲቡ ስሬ ወረዳ ለሊሳ ቀበሌ አርሶ አደር ዱላ ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት፣ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመደራጀት በኩታ ገጠም ቡና ማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ቡናን በስፋትና በጥራት እያመረቱ ከዘርፉ ልማት ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ገልጸው የግብርና ባለሙያዎችም ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን አንስተዋል።

ሌላኛው የቀበሌው አርሶ አደር አስፋው ገቢሳ፤ በቡና ምርት ላይ ከተሰማሩ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት ደግሞ ከሌሎች 40 የሚጠጉ አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ከ64 ሺህ በላይ የቡና ችግኝ መትከላቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.