የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

 ጤፍን በኩታ ገጠም ማልማታችን ምርታማነታችንን አሳድጎልናል- አርሶ አደሮች 

Sep 30, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ሰቆጣ ፤ መስከረም 19/2018(ኢዜአ)፡-ጤፍን በኩታ ገጠም ማልማታቸው ምርታማነታቸው እንዲያድግ ማስቻሉን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰቆጣ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።

በአስተዳደሩ በሰቆጣ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የጤፍ ማሳ የመስክ ጉብኝት ተካሄዷል።

በሰቆጣ ወረዳ የወለህ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሃብቴ ስዩም በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት የኩታ ገጠም አሰራር የግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደጉ ምርታማነታቸው እንዲጨምር አድርጓል።


የኩታ ገጠም አሰራሩ ሰብሉን በወቅቱ በማረምና የተባይ መከላከልና ቁጥጥር ስራን በጋራ በማካሄድ የጊዜ፣ ጉልበትና የገንዘብ ወጪን ለመቀነስ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጌታወይ አዳነ በበኩላቸው ጤፍን በኩታ ገጠም ማልማት በመቻላቸው የተሻለ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።


ባለፉት ዓመታት ያገኙትን ተሞክሮ በማስፋትም በጋራ በመስራት ከጤፍ ሰብላቸው ከፍተኛ ምርት እንደሚጠብቁ አስረድተዋል።

"ጤፍን በኩታ ገጠም ማልማት የሚያስገኘውን ከፍተኛ ጥቅም ከመስክ ምልከታው ለመገንዘብ ችያለሁ" ያሉት ደግሞ የፃግብጅ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አብርሃ ጉለሽ ናቸው።


በመስክ ምልከታው ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ አጎራባች አርሶ አደሮችን በማሳመን በቀጣይ የዘር ወቅት የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን ለመተግበር ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሞገስ ሃይሌ፤ ለዘንድሮው የምርት ዘመን በአራት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሽላና ዳጉሳ በኩታ ገጠም ማልማት ተችሏል ብለዋል።

አሰራሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂንና ግብዓትን ለአርሶ አደሩ በቀላሉ በማቅረብና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት አጋዥ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።


"የአርሶ አደሩ በኩታ ገጠም የማልማት ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል" ያሉት አቶ ሞገስ በዘንድሮው ክረምት በኩታ ገጠም ከለማው መሬትም ከ139 ሺህ 160 ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

የዛሬው የመስክ ምልከታም የኩታ ገጠም አሰራርን ያልተገበሩ አካባቢዎች ልምድ እንዲያገኙና አሰራሩን ለተገበሩት ደግሞ በምርት አሰባሰብ ሂደት ላይ ብክነት እንዳይኖር እገዛ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

በዛሬው እለት በተካሄደው የመስክ ምልከታ ላይም አርሶ አደሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.