የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን የሚያስችላትን ውጤታማ ድርድር አድርጋለች

Sep 30, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2018(ኢዜአ)፦ ስድስተኛው የስራ ላይ የቡድን ስብሰባ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን የሚያስችላትን ውጤታማ ድርድር ያደረገችበት መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት በስዊዘርላንድ -ጄኔቫ የተደረገውን ስድስተኛ ዙር የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከ23 ዓመታት በላይ ድርድር ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ በታዛቢነት በቆየችበት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ስድስተኛ ዙር የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ ላይ መድረሷን ገልጸዋል።

የዓለም የንግድ ድርጅት የዓለምን 95 በመቶ ህዝብ የያዙ 166 ሀገራትን ያቀፈ መሆኑን ገልጸው፤ ሀገራቱ 98 በመቶ የዓለምን የንግድ ሥርዓትን የሚያንቀሳቅሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት የስራ ላይ ቡድን ስብሰባ የባለብዙ ወገን ድርድሮች የሚያልቁበት ሂደት መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ሁለት ጊዜ የስራ ላይ ቡድን ስብሰባዎች ማድረግ መቻሏን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለዚህ ስኬት የበቃችው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ባስገኙት ለውጥ፣ የፋይናንስ ስርዓቱ ክፍት በመደረጉና እንደሀገር በተመዘገቡ ለውጦች መሆኑን አስታውቀዋል።

በዓለም የንግድ ድርጅት አምስተኛው የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሰጡ ሀገራት 20 እንደነበሩ አስታውሰው፤ በስድስተኛው ስብሰባ ወደ 30 ሀገራት ከፍ ማለታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዓለም ባንክም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን ድጋፍ መስጠቱን ተናግረዋል።

በስድስተኛ ዙር የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ ከ200 በላይ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ እንደተሰጠባቸው ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በዚህም ኢትዮጵያ ለድርጅቱ አባልነት መቃረቧን የሚያሳይ አመርቂ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፍሬ ነገር ሪፖርት ወደ ሥራ ቡድን ረቂቅ ሪፖርት ማደጉን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ሂደቱ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የተጀመረው የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ድርድር በትጋትና ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት ህግጋትና ለአባልነት የሚያበቁ መስፈርቶችን ማሟላት የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወኗን ገልጸው፤ የዳበረ ይዘትና የጊዜ ሰሌዳን ያካተተ የአባልነት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቷን አስታውቀዋል፡፡

በስድስተኛው የስራ ላይ ቡድን ስብሰባ ከስድስት ሀገራት ጋር የገበያ ዕድል ድርድር በማድረግ ሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡

ሰባተኛው የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ በጥር ወር 2018 ከተካሄደ በኋላ በካሜሮን በሚካሄደው 14ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት ስብሰባ አባል ለመሆን የሚያስችል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.