የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ስራዎች በዘርፉ ከፍተኛ አቅም እየፈጠሩ ነው - ቱሪዝም ሚኒስቴር

Oct 11, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ መስከረም 30/2018 (ኢዜአ)፡- አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎች የቱሪስት ፍሰቱን ከመጨመር ባሻገር በዘርፉ ከፍተኛ የገበያ አቅም እየፈጠሩ እንደሚገኙ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በመክፈቻ ስነ ሥርዓቱ መንግስት የኢትዮጵያን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ በ2018 በጀት ዓመት በልዩ ልዩ መስኮች የያዛቸውን እቅዶች ለሁለቱ ምክር ቤቶች አቅርበዋል።

በንግግራቸው መንግሥት ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት በመስጠት አዝጋሚ የነበረውን ጉዞ ወደ ጉልህ የእድገት አንቀሳቃሽ ሞተር መለወጥ መቻሉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የተዋበች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስፋፋት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት መንግስት ቱሪዝምን እንደ ትልቅ የኢኮኖሚ መስክ በመውሰድ ዘርፉን የሚያነቃቁ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶች የታደለች ብትሆንም ዘርፉ ለረጅም ዘመናት ተገቢውን ትኩረት ሳያገኝ በመቆየቱ በአግባቡ ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሀገሪቱ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ሀብት ለማስተዋወቅ የሚያግዝ የቱሪዝም ስትራቴጂ ማዘጋጀቷ በመስኩ በርካታ ለውጦች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን አንስተዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት እና ነባር የቱሪስት መስህቦችን የማደስና የመንከባከብ ስራ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።

ይህም የጎብኚዎችን ፍላጎት በማሳደግ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ እንዲያድግ ማድረጉን ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማስፋፋትና ከአፍሪካ ሃገራት የሚደረጉ የቱሪስት ፍሰቶችን ማሳደግ ተገቢ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው እንደገና አበበ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

በቀጣይ ኢትዮጵያን የሚያቋርጡ ተጓዥችን በስቶፕ ኦቨር (የእግረ መንገድ ቱሪዝም) በመጠቀም ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.