🔇Unmute
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2018 (ኢዜአ):- በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የንጋት ሰው ሰራሽ ሐይቅ ላይ 70 የሚደርሱ የወጣት ኢንተርፕራይዞች በዓሳ ማስገር ተደራጅተው እየሰሩ እንደሚገኙ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ - የንጋት ሐይቅ የረቂቅ ማስተር ፕላን ጥናት ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት÷ ሕዳሴ ግድብ የፈጠረው የንጋት ሐይቅ ለበርካታ ዜጎች በረከት መሆን ጀምሯል ብለዋል።
የንጋት ሐይቅ አሁን ላይ በዓመት ከ15 ሺህ ቶን በላይ ዓሳ ማምረት የሚያስችል አቅም እንዳለው ጠቅሰው በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 5 ሺህ ቶን የዓሳ ምርት ለገበያ መቅረቡን ገልጸዋል።

የሐይቁን ከፍተኛ የዓሳ ምርታማነት አቅም ለማሳደግ የንጋት የተቀናጀ ማስተር ፕላን ዝግጅት የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎችን እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በንጋት ሐይቅ ላይ ለዓሳ ማስገር ስራ አስፈላጊ መሳሪያዎች የተሟሉላቸው 70 የሚደርሱ የወጣት ኢንተርፕራይዞች ስራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው÷ ለንጋት ሐይቅ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ዝግጅትና ትግበራ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የንጋት ሐይቅ የ240 ኪሎ ሜትር የውሃ አካልና ከሰባ በላይ ደሴቶች ለትራንስፖርት፣ ለዓሳ ምርታማነትና ለሆቴልና ቱሪዝም ልማት ምቹ መሆኑን በመጥቀስ ለበርካታ ወጣቶች መልካም ዕድል ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።
በሕዳሴ ግድብ የተፈጠረው የንጋት ሐይቅ ላይ በዓሳ ማምረት የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው በርካታ ወጣቶች ሃብትና ጥሪት እያፈሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከውሃና ኢንርጂ፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረው የንጋት ሐይቅ የተቀናጀ አስተዳደር ማስተር ፕላንም ስኬቶችን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ደበበ ደፈርሶ÷ ማስተር ፕላኑ የንጋት ሐይቅ የፈጠራቸውን ጸጋዎች በሥርዓት ለማስተዳደር ታልሞ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

የንጋት ሐይቅ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የዓሳ ሃብት፣ የትራንስፖርትና ተያያዥ ትሩፋቶች ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።
ማስተር ፕላኑም ቀጣይ የሚፈጠሩ ከተሞችን ታሳቢ በማድረግ የንጋት ሐይቅ የውሃ ሃብትና ከባቢውን በመጠበቅ የተፋሰሱን ሀገራት የውሃ ሃብት ዘላቂነት የሚያስጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የከተማ ፕላንና ዲዛይን ክፍል ኃላፊ ይኸነው ኃይሉ÷ የማስተር ፕላን ዝግጅቱ የንጋት ሐይቅ የቱሪዝም፣ ከተማ ልማት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት መሠረተ ልማትን ለማዘመን ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025