የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ረቂቅ አዋጁ የግብርና ኤክስቴንሽንን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ነው

Oct 23, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 12/2018(ኢዜአ)፦የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ዘርፉን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋዊ የባለድርሻ አካላት ውይይት አካሂዷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀው ከኢትዮጵያ የግብርና ዕድገት ጋር የሚራመድ የግብርና ኤክስቴንሽን ህግ በማስፈለጉ ነው፡፡


በረቂቅ አዋጁ ላይ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የረጅም ጊዜ ውይይትና ጥናት መደረጉን ገልጸው፤ በዚህም ከዘርፉ ተዋንያን ገንቢ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፤ በግብዓትነትም ተካተዋል ብለዋል፡፡

የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ዘርፉን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) መንግስት የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የሚፈለገውን ዕድገት ለማስመዝገብ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ በዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥ እና አስተዳደር ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ያስችላል ብለዋል፡፡

በግብርና ኤክስቴንሽን ዘርፍ በመንግስት ብቻ ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራት ላይ ሌሎችም የዘርፉ ተዋንያን እንዲሳተፉ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ ዘርፉ ራሱን በቻለ ህግ እንዲመራ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ የአርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ፍላጎት መነሻ በማድረግ ተሞክሮዎችን በሚያሰፋ መልኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡


የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ልምድና እውቀት የያዘ መሆኑን ገልጸው፤ የምግብ ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.