የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን በባቡር መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የያዘችውን እቅድ ይደግፋል

Oct 27, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 16/2018(ኢዜአ):-የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካን በባቡር መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የያዘችውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ በህብረቱ የመሰረተ-ልማትና ኢነርጂ ዘርፍ ኮሚሽነር ለሬቶ ማታቦጅ ገለጹ፡፡

በአፍሪካ ህብረት የመሰረተ-ልማትና ኢነርጂ ዘርፍ ኮሚሽነር ለሬቶ ማታቦጅ ለኢዜአ እንደገለጹት፥የባቡር መሰረተ ልማቶች አህጉሪቱን እርስ በእርስ ለማስተሳሰር፣ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ለወጪና ገቢ ንግድ መሳለጥና ለቀጣናዊ ትስስር ቁልፍ መሳሪያ ናቸው።

የባቡር መሰረተ ልማት ሸቀጦችንና ሰዎችን በብዛት፣በፍጥነትና በጥራት ለማጓጓዝ ያለው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ህብረት ንግድንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያሻሽሉ የባቡር መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የባቡር ትራንስፖርትን ለማስፋፋት እየወሰደቻቸው ያሉ እርምጃዎች ከራሷ አልፎ ለአፍሪካ ተሞክሮ እንደሚኖረውና አርአያ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የትራንስፖርት ኮሪደሮችን ለማጠናከር የጀመረችው ተግባር ለአህጉራዊ ንግድ እና የሰዎችን እንቅስቃሴ ለማሳለጥ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ያምናል ብለዋል፡፡

ህብረቱ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 የልማት እቅዶችን ለማሳካት በኢትዮጵያ የባቡር ፕሮጀክቶችን ጨምሮ አህጉሪቱን ለሚያስተሳሰር የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ለአፍሪካ እድገትና ብልጽግና የባቡር ትራንስፖርት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተው፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የጀመረችው ተግባር ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

ተግባሩን ለመደገፍ ህብረቱ የቴክኒክ ፣ፋይናንስ ማሰባሰብ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.