🔇Unmute
ሚዛን አማን ፤ ጥቅምት 18/2018(ኢዜአ)፦መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከልን በማስፋፋት የመንግስት አገልግሎቶችን ፍትሃዊነትና ተጠያቂነት የማረጋገጡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ማዕከሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እና የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መሰለ ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ እንዳሉት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ለዜጎች የሚሰጡ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማዘመን እና ግልጽ ለማድረግ የሚያስችል ነው።

የማዕከል ግንባታ ሥራው በፌዴራል ደረጃ ከተጀመረ በኋላ በክልሎች እየተስፋፋ መምጣቱን ገልጸው፣ ዛሬ የተመረቀውን የሚዛን አማን ማዕከልን ጨምሮ በስምንት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የማስፋፋት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በእነዚህ ማዕከላት ዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶችን በፍትሃዊነት፣ በፍጥነት፣ በክብርና ተጠያቂነት ባለው ሁኔታ በአንድ ቦታ እንዲያገኙ መደረጉንም ምክትል ኮሚሽነሯ አመልክተዋል።
በቀጣይ ማዕከሉን በሁሉም የመንግሥት መዋቅር ዕርከኖች የማስፋፋቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ አገልግሎቱ የሀገራዊ የሪፎርም ሥራ ስኬት አንዱ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳለጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚሰጥ በመሆኑ ዜጎች ፈጣን ምላሽ በማግኘት ጊዜያቸውን ለልማት እንዲያውሉ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚዛን አማን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መገንባቱንና 32 አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
የማዕከሉ አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ እንዲጠናከርና እንዲሻሻል ክልሉ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል።
በተያዘው ዓመትም በክልሉ አምስት ከተሞች የዞንና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮችን በማስተባበር ተመሳሳይ ማዕከል የመገንባት ሥራ እንደሚሠራም ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር) አመልክተዋል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025