🔇Unmute
አምቦ ፤ጥቅምት 20/2018(ኢዜአ)፡- በአምቦ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከተማዋን አዲስና ውብ ገጽታ እንዳላበሳት የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የኮሪደር ልማት ስራ በስፋት እየተከናወነባቸው ከሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች መካከል አንዷ የአምቦ ከተማ ናት።

በከተማው የተከናወነውን የኮሪደር ልማት አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ በፊት ያላትን ገጽታ እየቀየረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአምቦ ከተማ ነዋሪ አቶ መንግስቱ ረጋሳ እንዳሉት፤ ኮሪደሩ ከመጀመሩ በፊት ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፈው ዋና መንገድ በትራፊክ እና በሰዎች እንቅስቃሴ እጅግ የተጨናነቀ ነበር።

የኮሪደር ልማት ስራው ከተከናወነ ወዲህ ግን መንገዱ እንዲሰፋ በመደረጉ ለተሽከርካሪ እና ለሰዎች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባለፈ የከተማዋን ውበት ጨምሯል ብለዋል።
በዋና መንገዱ ግራ እና ቀኝ ሰዎች ያለ ስጋት የእግር ጉዞ እያደረጉበት ጤናቸውን እየጠበቁ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቅሰው ወጣቶች የመዝናኛ እና የማረፊያ ስፋራ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ መንጌ ተፈሪ፣ የከተማው ኮሪደር ልማት ሳይጀመር በፊት በመንገድ ዳር ላይ የተከማቹ ደረቅ ቆሻሻዎች መንገድ ላይ ለማለፍ ምቹ ሁኔታ አይፈጥሩም ነበር ብለዋል።

አሁን ላይ ቆሻሻ ስፍራዎቹ ወደ መዝናኛ ቦታነት መቀየራቸውን ተናግረው ለኮሪደር ልማቱ ስኬታማነት ከከተማው አስተዳደር ጎን በመቆም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በተሰራው የኮሪደር ልማት አካባቢው በንጹህ አየር ስለተሞላ ከተማዋን ለመኖር ምቹ እና ጽዱ አድርጓታል ሲሉም ተናግረዋል።

ወጣት ባይሳ ታምሩ በበኩሉ፤ የሃገር እድገትን ለማፋጠን የወጣቶች ሚና ሰፊ መሆኑን ጠቅሶ፤ በከተማው እየተካሄደ ያለው ልማት እንዲፋጠን በንቃት እንደሚሳተፍ ገልጿል።

የኮሪደር ልማት ስራው የከተማዋን ገፅታ በመቀየር ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ምቹ እንደሚያደርጋት ገልጾ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን የልማት ስራው እስከሚጠናቀቅ የድራሻውን እንደሚወጣም አረጋግጧል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025