🔇Unmute
ነቀምቴ፤ ጥቅምት 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የወጠነቻቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ሀገራዊ እድገትን በማፋጠን ትልቅ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችሉ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ የተደረጉት የጉባ ላይ ብስራቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት በማሳለጥ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌትነቷን እውን የሚያደርጉ እንደሆኑ መገለጹ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ በሂደት ላይ ያሉ እነዚህ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ቀጣይ እጣ ፈንታዋን የሚወስኑ መሆናቸውን አፅንኦት ሰጥተዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን እንዳሉት ኢትዮጵያ የወጠነቻችው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ከድህነት ለመውጣት የተጀመረውን ጉዞ የሚያፋጥኑ ናቸው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በዚህ ዓመት ሥራ የጀመሩና በውጥን ላይ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ሀገራዊ እድገትን ማፋጠን ብቻ ሳይሆን ሀገራችንን ከአደጉ ሀገራት ተርታ የሚያሰልፉ ናቸው ብለዋል።

በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ጌታቸው መኛር(ዶ/ር)፤ በመንግስት እየተተገበሩ ያሉ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጦች የኢትዮጵያን ፈጣን እድገት እውን የሚያደርጉ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
መንግስት ከአነስተኛና መካከለኛ ፕሮጀክቶች በላይ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ማተኮሩ በአጭር ጊዜ ከድህነት ለመውጣት መንገድ የሚጠርግ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም መንግስት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት በመለየት እንደየ አስፈላጊነቱ ወደ ልማት መግባቱ አዲስ ልምምድ መሆኑን አስታውሰው፣ ጅምር እንቅስቃሴው መሰረታዊ እድገትን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን በተጀመረው አካሄድ በሁሉም ዘርፍ ያሉትን አቅሞች አሟጦ በመጠቀም የዜጎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጡ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
ግዙፍ መሰረታዊ ፕሮጀክቶቹ የሀገርን ብሔራዊ ገፅታ የሚቀይሩ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነቷን በማሳደግ ተፅእኖ ፈጣሪነቷን ያጎላል ብለዋል።

ሌላው በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ገመቹ ሙላቱ(ዶ/ር) በበኩላቸው የግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለሀገርና ለዜጎች ዘርፈ ብዙ ትሩፋት ይዘው ይመጣሉ ነው ያሉት።
በተለይም ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸው፣ ወጣትና አምራች የሆነውን የሰው ሀይል ውጤታማ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
ከሁሉም በላይ እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ፈጣን የእድገት ጉዞ በማስቀጠል ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025