🔇Unmute
ጭሮ፤ ጥቅምት 22/2018(ኢዜአ)፡- በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ የግብርና ስራቸው ላይ በመትጋት ከተረጂነት ወጥተው ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የወረዳው አርሶ አደሮች ለረጅም ዓመታት በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ታቅፈው ሲደገፉ መቆየታቸውን አስታወሰው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባከናወኑት የግብርና ልማት ስራ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፈው ሀብት በማፍራት የተሻለ ኑሮ መምራት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ከአርሶ አደሮቹ መካከል በጭሮ ወረዳ የአርበረከቴ ቀበሌ ነዋሪ ፎዚያ መሐመድ እንዳመለከቱት፤ ቀደም ሲል ከነቤተሰባቸው ለችግር በመጋለጣቸው ለዓመታት በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ታቅፈው ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን በሁለት ጥማድ ማሳ ላይ ማምረት የጀመሩትን ሽንኩርት ለጭሮና ሂርና ከተሞች ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
"ባለፈው ዓመት ካለማሁት ሽንኩርት 40 ኩንታል ምርት ለገበያ አቅርቤያለሁ" ያሉት አርሶአደሯ ፤ ገቢያቸው እያደገ በመምጣቱ ተጨማሪ ማሳ በመከራየት ልማቱን በማስፋፋት ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።
መንግስት ከተረጂነት እንዲወጡ በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ እና የብድር አገልግሎት በፍየል እና ዶሮ እርባታ ስራ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ የቀበሌው አርሶ አደር ትዕግስት ባህሩ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፈው 120 ሺህ ብር መቆጠብ መቻላቸውን ጠቅሰው፤ ገቢያቸው እያደገ ኑሯቸውም እየተሻሻለ መምጣቱን አብራርተዋል።
አርሶ አደር አይሻ አብዶ እንዳሉት፤ ከሌሎች 20 ሴቶች ጋር በመደራጀት በተመቻቸላቸው ከ200 ሺህ ብር ብድር በጓሮ አትክልት ልማት እና ፍየል እርባታ ተሰማርተው ገቢያቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ።
የካሮት እና ሽንኩርት ምርት ለገበያ በማቅረብ በዓመት እስከ 100 ሺህ ብር ማግኘት መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም ከተረጂነት ተላቀው የተሻለ ኑሮ እየመሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ የጀመሩትን የጓሮ አትክልት ልማት በማስፋፋት ጥቅል ጎመን እና ሽንኩርት ምርት ለገበያ በማቅረብ ገቢ እያገኙ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አርሶአደር ዘይኑ ዩሱፍ ናቸው።
በአንድ ወቅት ለገበያ ከሚያቀርቡት ሽንኩርት እስከ 50 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከሚያለሙት የግብርና ምርቶች እያገኙ ያለው ገቢ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ሀብት በማፍራት አኗኗራቸውን መቀየር እንዳስቻላቸው አርሶ አደሩ ተናግረዋል።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ቡድን መሪ አቶ ታጁዲን ሁሴን ፤ በዞኑ 15 ወረዳዎች በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ታቅፈው ከነበሩ 69 ሺህ 360 የቤተሰብ መሪዎች መካከል ከ48 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ የምግብ ዋስትናቸውን አረጋግጠዋል ብለዋል።
አርሶአደሮቹ መንግስት ራሳቸውን እንዲችሉ ባመቻቸለቸው የብድር አገልግሎት በእርሻ ስራ፣ በችግኝ ዝግጅት፣ በእንስሳት እርባታና ሌሎች ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን አመልክተዋል።
መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ዜጎች ከተረጂነት መውጣት እንዲችሉ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025