የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በምዕራብ ጎንደር ዞን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማነቃቃት እየተሰራ ነው

Nov 6, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ገንዳውኃ፤ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ጎንደር ዞን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማነቃቃት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።

አበዳሪ ተቋማትን፣ የኢንቨስትመንት ፎካሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈና ዘርፉን ለማነቃቃት ያለመ የምክክር መድረክ በገንዳውኃ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

በዞኑ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መሰንበት መልካሙ እንደገለጹት በዞኑ በጸጥታ ችግር ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እየተሰራ ነው።

ዞኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ሰፋፊ መሬትና ተስማሚ የአየር ንብረት እንዳለው ገልፀው የዛሬው መድረክም በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም ተከትሎ አዳዲስ አልሚዎችን ለመሳብና ነባር ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማነቃቃት የብድር አቅርቦትና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በማለም መሰናዳቱን አብራርተዋል።

የገንዳ ውኃ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ታድሎ አቡሃይ እንዳሉት በከተማው 134 ሄክታር የሚጠጋ ቦታ ለኢንዱስትሪ ፓርክ ተለይቶ መሰረተ ልማት የማሟላት ስራ ተሰርቷል።

እስካሁን ከ14 በላይ የሚሆኑ ባለሀብቶች ማሸነሪ በመትከል እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመው ወደ ስራ ያልገቡትን በመደገፍ ወደ ተግባር ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የዋሊያ ካፒታል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ብርሃኑ ስመኘው በበኩላቸው በዞኑ የሚካሄደውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ለአልሚ ባለሃብቶች የግብርና ግብዓቶችን፣ የሰሊጥ ማበጠሪያና ዘመናዊ መውቂያ ማሽኖች እየቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የካፒታል እቃዎች ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገንዳውኃ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ደመወዝ ምትኩ በበኩላቸው የአካባቢውን ፀጋ ለማልማትና ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር ብድር በማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በውይይቱ ላይም አመራሮች፣ ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.