🔇Unmute
ሚዛን አማን ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦የሚዛን አማን ከተማን ገጽታ ይበልጥ የሚያጎላ ከ4 ኪሎ ሜትር በላይ የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
በሀገሪቱ ዜጎችን ለመጪው ዘመን የከተሜነት ኑሮ ማዘጋጀትን ታሳቢ አድርጎ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የበርካታ ከተሞችን ገጽታ በመለወጥ ለኑሮ ምቹና ሳቢ እንዲሁም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያስቻለ ነው።

በበርካታ ከተሞች ተግባራዊ የሆነው የኮሪደር ልማት ከገጽታ ግንባታ ባሻገር የትራፊክ አደጋን በመቀነስ፣ በሥራ ዕድል፣ ለማህበረሰቡ አማራጭ የመዝናኛ ስፍራ በመፍጠር ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
የኮሪደር ልማት እየተከናወነባቸው ካሉ ከተሞች አንዷ በሆነችው ሚዛን አማንም ልማቱ በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ እየተተገበረ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ ሁለተኛው ምዕራፍ የሆነውና 4 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የኮሪደር ልማት ግንባታ በመፋጠን ላይ ነው።

የግንባታ ሥራው በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን የከተማዋን ውበትና ገጽታ ይበልጥ ከማሻሻል ባለፈ ለኑሮ ምቹ እንደሚያደርጋትም ተመላክቷል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅና የግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ወንድሙ አለማየሁ፣ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ተወዳዳሪና ለኑሮ ምቹ እያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በኮሪደር ልማት የቆሻሻ መጣያ የነበሩና ለኑሮ አመቺ ያልነበሩ አካባቢዎች ጭምር ከመልማታቸው ባለፈ መንገዶች እግረኛና ተሽከርካሪን ታሳቢ በማድረግ ሰፍተው በመሰራታቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸዋል።
ልማቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት አቶ ወንድሙ፣ በአሁኑ ወቅት የከተማዋን ውበትና ገጽታ ይበልጥ የሚያሻሽልና ከ4 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ግንባታ በሁለተኛ ምዕራፍ እየተፋጠነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ልማቱ አረንጓዴ መናፈሻ፣ የእግረኛና የሳይክል መንገድ እንዲሁም ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራትን በማካተት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ ለልማቱ እያደረገ ያለው ትብብር ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ወንድሙ፣ ለዚህም በአሁኑ ወቅት ከሚከናወነው 4 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት 1 ነጥበ 6 ኪሎ ሜትሩ በማኅበረሰቡ ሙሉ ተሳትፎ የሚሠራ ነው ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪ አቶ ዓለሙ ባቹብ በበኩላቸው እንዳሉት የኮሪደር ልማት ሥራው የሚዛን አማን ከተማን ውበት ከማጉላት ባሻገር በከተማዋ ይስተዋል የነበረን የእግረኛ መንገድ ጥበት ችግር እየፈታ ነው።

ከመጀመሪያ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ማህበረሰቡ በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፣ አሁን በግንባታ ሂደት ላይ ላለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ስኬታማነት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025