የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በነቀምቴ ከተማ ስራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተው በተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው

Nov 7, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ነቀምቴ፤ ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፡- በነቀምቴ ከተማ ስራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተው በተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን የከተማዋ የስራ እድል ፈጠራ እና ክህሎት ፅህፈት ቤት ገለጸ።

የነቀምቴ ከተማ የስራ እድል ፈጠራ እና ክህሎት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መልካሙ ሙለታ እንደገለፁት በከተማዋ የሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን እንዲጠቅሙ ጥረት እየተደረገ ነው።

በተያዘው በጀት ዓመትም 22 ሺህ 300 ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ በመጀመሪያው ሩብ አመት 2 ሺህ 600 ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተፈጠረ ምቹ ሁኔታም ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሰጠቱን ጠቅሰው የተደራጁ ወጣቶችም በተሰጣቸው የመስሪያ እና መሸጫ ሼዶች ስራ እየጀመሩ መሆኑን አንስተዋል።

ወጣቶቹ ወደ ስራ የገቡትም በእንስሳት እርባታ፣ በዶሮ እርባታ፣ የንብ ማነብ እና ሌሎች ስራዎች መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ስራ የገቡ ወጣቶችም በሚያመርቱት ምርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የገበያ ትስስር እንዲፈጥርላቸው ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በከተማው የጨለለቂ ቀበሌ ተወካይ ወይዘሮ ሜሪ ጃለታ፣ በቀበሌው ከ185 በላይ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ወደ ስራ ለገቡ ወጣቶችም የብድር አገልግሎት፣ ስልጠና፣ የመስሪያ እና የመሸጫ ቦታ ድጋፍ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች ተደርጎላቸዋል ነው ያሉት።

በዚሁ ቀበሌ በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ ከገቡት መካከል ሀብሌ ሰዒድ፤ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመደራጀት የዶሮ እርባታ ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

አንድ ሚሊየን ብር ብድር ተሰጥቷቸው 3 ሺህ የአንድ ቀን ጫጩት እና 600 የእንቁላል ዶሮዎች አስገብተው ስራ መጀመራቸውን ገልጸው የከተማው የስራ እድል ፈጠራ እና ክህሎት ፅህፈት ቤት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንዳደረገላቸው አውስተዋል።

እስካሁንም በሶስት ዙር እንቁላል ለገቢያ አቅርበው ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን አስረድተዋል።

ሌላኛው የስራ እድል ተጠቃሚ ጌታሁን ሀይሉ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመደራጀት በወተት ላሞች እርባታ እና ከብት ማድልብ ስራ ዘርፍ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

በተሰጣቸው 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ብድር 20 የወተት ላሞች እና የሚደልቡ ከብቶችን በማስገባት ራሳቸውን ለመለወጥ እየተጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.