🔇Unmute
ወልድያ፤ጥቅምት 28/2018 (ኢዜአ)፦በሰሜን ወሎ ዞን የቡና ልማትን ለማስፋፋት በተሰጠው ትኩረት ከ47 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በልማቱ እየተሳተፉ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት ለቡና ልማት በተሰጠው ትኩረትም 1 ሺህ 419 ሄክታር መሬት በክላስተር እየለማ መሆኑም ተመላክቷል።
በመምሪያው የፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ፋሪስ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ አርሶ አደሩ ከሰብል ምርቱ ጎን ለጎን በቡና ልማት በመሰማራት ተጨማሪ ሃብት እንዲያፈራ እየተሰራ ነው።
በዚህም በዞኑ የቡና ልማትን ለማስፋፋት በተሰጠው ትኩረት 47ሺህ 600 አርሶ አደሮች በልማቱ እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸው፥ከልማቱም በዘንድሮ ዓመት ብቻ 12ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።
ከቡና ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግም በአሁኑ ወቅት በመጪው ክረምት የሚተከሉ 500 ሺህ የቡና ችግኞችን የማፍላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የቡና ልማቱ በዞኑ ሥር ባሉ ሐብሩ፣ ጉባላፍቶ፣ ራያ ቆቦ፣ ላስታና መቄት ወረዳዎች እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፥የቡና ልማት ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የባለሙያ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በሐብሩ ወረዳ የቡሆሮ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለበል ሽፈራው በበኩላቸው እንደገለጹት ባለፉት አምስት ዓመታት በባለሙያዎች እገዛ ቡናን በሳይንሳዊ መንገድ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ካለሙት የቡና ተክልም ስድስት ኩንታል ቡና በማምረት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ አቅርበው ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አስረድተዋል።
በ1ሺህ 500 ካሬ መሬት ላይ ከለሙት የቡና ተክል ሦስት ኩንታል የቡና ምርት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በጉባላፍቶ ወረዳ የጌሾበር ቀበሌ ነዋሪ አስማማው ኃይሉ ናቸው።
የቡና ተክል በተባይና በውርጭ እንዳይጎዳ የዘርፉ ባለሙያዎች የቅርብ ክትትል እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸው፥ ይህም በልማቱ ስኬታማ እንዲሆኑ የጎላ አስተዋጾ ማድረጉን ተናግረዋል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025