የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገና መንግስት ለታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃና ልማት የሰጠውን ልዩ ትኩረት ማሳያ ነው

Nov 13, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ጎንደር ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ጥገና ሥራ መንግስት ለታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃና ልማት የሰጠውን ልዩ ትኩረት ያሳያል ሲሉ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝምና ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ሃላፊና ተመራማሪ የሺዋስ አቡኔ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የሺዋስ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዘመን ተሸጋሪ ታሪካዊ ቅርሶች የአንድ ሀገርና ህዝብ የማንነት መገለጫዎች ከመሆን ባለፈ የኢኮኖሚ መሰረት ነው።


መንግስት ለዓለም አቀፍ ቅርሱ ትኩረት ሰጥቶ ያከናወነው የእድሳትና ጥገና ሥራ የህዝብና የሀገርን ታሪክ፣ ባህል፣ እሴትና ማንነትን ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።


ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ ቅርሶች የህዝቦች የአብሮነትና የጋራ ትርክት መገንቢያ አሻራዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የጥገና ሥራው ዓለም አቀፍ የቅርስ ጥገና ሳይንስ መስፈርቶችን መሠረት ማድረጉ ዘላቂ እድሜ እንዲኖረው ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል።

የህዝቦችን ታሪክ፣ ባህል፣ እምነት፣ ትውፊት፣ ጥበብና ስልጣኔን አጣምረው የያዙ ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ለትውልድ እንዲሻገሩ ለማድረግ በለውጡ መንግስት የተጀመሩ ተግባራት ፋና ወጊ መሆናቸውንም የሺዋስ (ዶ/ር) አመልክተዋል፡፡

የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስቱ ለበርካታ ዓመታት በጥገና እጦት አደጋ ውስጥ የቆየ ዓለም አቀፍ ቅርስ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን መታደሱ መንግስት ለዘመን ተሻጋሪ ቅርሶች ጥበቃና ልማት የሰጠውን ልዩ ትኩረት ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል፡፡


እንደ የሺዋስ (ዶ/ር) ገለጻ ጎንደር የበርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኗ የአብያተ መንግስቱ ጥገና ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉ የቱሪስት ፍሰቱን በማሳደግ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት በኩል ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቅርሶች ደህንነትና ጥበቃ ላይ የጥናትና ምርምር ተግባራትን ሲያከናወን መቆየቱን አስታውሰው፤ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራትም ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡


ዓለም አቀፍ ቅርሱን ከአደጋ ለመጠበቅ መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች ወሳኝና ወቅታዊ መሆናቸውን ጠቁመው ህዝቡና ባለድርሻ አካላት የቅርሱን ደህንነት በዘላቂነት በመጠበቅ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ "የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት አልታደሰም፤ አልተጠገነም ዳግም ተወለደ እንጂ" በማለት የዓለም አቀፍ ቅርሱን ዳግም ትንሳኤ በቦታው ተገኝተው ማብሰራቸው የሚታወስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.