የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኮሚሽኑ ተኪ ምርቶች ላይ እየሰራ ያለውን ውጤታማ ተግባራት የበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል 

Nov 21, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

አዲስ አበባ፤ሕዳር 11/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ እና ተኪ ምርቶች ላይ እየሰራ ያለውን ውጤታማ ተግባራት የበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የ2018 ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ ኮሚሽኑን የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት በሩብ ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ተናግረዋል።


በዚህም በሩብ ዓመቱ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ 961 ሚሊየን ዶላር ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

ይህም ከእቅዱ 81 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ7 ነጥብ 87 በመቶ እድገት እንዳለው አንስተዋል።

የተለያዩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት 211 ሚሊየን ዶላር ተኪ ምርት ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።

የወጪ ንግድ አፈጻጸም በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ከ39 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከ49 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

በሩብ ዓመቱ ለ123 የውጭ ባለሀብቶች ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን የሩብ ዓመት ሪፖርት ካደመጡ በኋላ የቋሚ ኮሚቴ አባላት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከማበረታታ አንጻር ምን አይነት ስራዎች እየተሰሩ ነው? የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መነቃቃት ትልቅ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።


ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በሩብ ዓመቱ በርካታ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመዋል።

የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አሻ ያህያ ፤ኮሚሽኑ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ እና ተኪ ምርቶች ላይ እየሰራ ያለውን ውጤታማ ተግባራት የበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


ኮሚሽኑ በሩብ ዓመቱ ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አንስተው የተጀመሩ አመርቂ ስራዎች በወጪ ምርቶች፣ በስራ እድል ፈጠራ፣በቀልጣፋ አገልግሎትና በሌሎችም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

በተለይ የወጪ ምርቶች መዳረሻ ቦታዎችን በማስፋት ላይ እንዲሁም ከገቡት ውል ውጪ ህገወጥ ተግባራት ላይ የተሳተፉ ባለሀብቶች ላይ ህጋዊ እርምጃዎች በተጠናከረ መልኩ ሊወሰዱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.