የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በሸገር ከተማ ባለፉት አራት ወራት ከ80 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል

Nov 21, 2025

IDOPRESS

🔇Unmute

ሸገር፤ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፡- በሸገር ከተማ በበጀት አመቱ ባለፉት አራት ወራት ከ80 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የከተማው የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የሸገር ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ተወካይ አቶ ድጋፈ ጸጋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማው ያለውን እምቅ አቅም በጥናት በመለየት ስራ አጥነትንና ድህንትን ለመቀነስ ቀጣይነት ያለው ስራ እየተሰራ ነው።

በበጀት አመቱ የስራ አጦችን ፍላጎትና ክህሎት በመለየት በማህበር በማደራጀትና በቅጥር የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፊ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በዚህም የከተማው ወጣቶች፣ ሴቶችና አርሶ አደሮች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ክህሎት መር ስልጠና መሰጠቱን አክለዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በከተማ አስተዳደሩ 310 ሺህ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴ ባለፉት አራት ወራት በኢንተርፕራይዞች በማደራጀትና በቅጥር ለ80 ሺህ 195 ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አብራርተዋል።


የስራ እድሉ የተፈጠረው በጎጆ ኢንዱስትሪ፤ በብረታብረት፤ በአልባሳት፣ በከብትና ዶሮ እርባታ፣ በወተትና የወተት ተዋጽኦ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በከተማ ግብርና ዘርፎች መሆኑን ገልጸዋል።

ለተጠቃሚዎችም በከተማው 58 ሄክታር የማምረቻ መሬት መቅረቡን ጠቅሰው፤ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ከባንኮችና ማይክሮ ፋይናንሶች ጋር ትስስር መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም የሳሙና፣ የመኖ ማቀነባበሪያ፣ የብሎኬት፣ የጋርመንትና የዳቦ ማምረቻ ማሽኖች በሊዝ ማሽን አሰራር መቅረቡን አንስተዋል።

የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድም ማህበራቱ ምርቶቻቸውን በባዛር፣ በኤግዚቢሽንና በእሁድ ገበያዎች እንዲያቀርቡ የተደረገ ሲሆን፤ በዚህም 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።


የስራ እድል ፈጠራው የስራ አጥነትና ድህንነትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው ገልጸው፤ ዜጎችን በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ ለማድረግ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም በሸገር ከተማ በመልካ ኖኖ፣ በለገ ጣፎ ለገ ዳዲ እና በኩራ ጅዳ ክፍለ ከተሞች ለዘመናዊ የገበያ ማዕከላት የሚውሉ ሶስት ባለ አራት ወለል ህንጻዎች ግንባታቸው በመገባደድ ላይ ናቸው ብለዋል።

በቀጣይም በፉሪ፣ በኮዬ ፈጬና ገላን ጉዳ ክፍለ ከተሞች የገበያ ማዕከላቱን የማስፋፋት ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.