🔇Unmute
አዲስ አበባ፤ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የዓሳ ሃብት ምርታማነትን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በእንስሳትና የዓሳ ሃብት ላይ ዕመርታዊ ለውጥ እንዲመዘገብ እያደረገ ይገኛል።
መርሃ ግብሩም በዋናነት የእንስሳት ተዋጽኦ ወተት፣ እንቁላል፣ ሥጋ፣ ማር እና የዓሳ ሃብት ምርታማነትን በማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለመ ሀገር አቀፍ የልማት ግብ ነው።
የምግብ ዋስትና እና ሥርዓተ ምግብን ማሻሻል፣ የእንስሳት ምርታማነትን ማሻሻል፣ በቤተሰብ ደረጃ በምግብ ራስን መቻል፣ በከተማና በገጠር የምርትና ገበያ ትስስርን በማሳለጥ የስራ ዕድል መፍጠር እንዲሁም ገቢ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የመርሃ ግብሩ ወሳኝ ዓላማዎች ናቸው።
በዚህም በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሻሻል የሸማቹን ማህበረሰብ የምርት ፍላጎት ምላሽ በመስጠት ተጨባጭ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)፤ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አካል በሆነው የዓሳ ሃብት ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወነ ተግባር በ2018 ዓ.ም በጀት ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ 48 ሺህ ቶን በላይ የዓሳ ሃብት ማምረት ተችሏል ብለዋል።
መደበኛ የዓሳ ሃብት ምርት አቅም ከሆኑ የውሃ አካላት በተጨማሪ በሰው ሰራሽ ኩሬዎች የዓሳ ምርታማነትን ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት እንዲመዘገብ እያስቻሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የዓሳ ሃብትን ለማሳደግ እየተከናወኑ በሚገኙ የልማት ስራዎችም በምርታማነት ዕድገት ላይ ዕመርታዊ ስኬት ማስመዝገብ እንደተቻለ አስረድተዋል።
በሩብ ዓመቱ 41 ሺህ ቶን ዓሳ ለማምረት ታቅዶ 48 ሺህ ቶን ማምረት ተችሏል ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው፤ አሁን ላይ የዓሳ ምርታማነትን በዓመት ከሶስት እጥፍ በላይ ማሳደግ እየተቻለ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የዓሳ ሃብት ምርታማነትን ለማሳደግም ነባር የዓሳ ጫጩት ማባዣ ማዕከላትን በማደስና ተጨማሪ ማዕከላትን በመገንባት የዓሳ ጫጩት የማሰራጨት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የዓሳ ምርት ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን በመገንባት ለዜጎች የሥራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የዓሳ ጫጩቶችን በማስራጨት ስራም የዓሳ ምርት የማይታወቅባቸው የኢትዮጵያ የውሃ አካላት ምርት የሚሰጡበትን ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት ከ13 ሚሊየን በላይ የዓሳ ጫጩት ለማሰራጨት በተያዘው ዕቅድ መነሻነት በሩብ ዓመቱ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን የዓሳ ጫጩቶችን ማሰራጨት እንደተቻለም አስታውቀዋል።
Jul 17, 2025
Apr 24, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፦ የሲሚንቶ ንግድ እና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተመለከተ የወጡ መመሪያዎች ገበያውን በማረጋጋትና የዋጋ ግሽበትን በመቀ...
Feb 12, 2025