የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

በከተሞች የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን የማዘመን ስራዎች ትኩረት ተደርጎባቸዋል

Jan 13, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2017(ኢዜአ)፦በከተሞች የትራንስፖርት መሰረተ ልማትን የማዘመን ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዘርፉ የስራ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

ሃላፊዎቹ በአስር አመት ውስጥ በሁሉም ከተማ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ የተያዘውን ውጥን ለማሳካት የሚያስችል ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን እንዳሉት ሀገሪቱ ባላት የታዳሽ ኃይል ሀብት ለመጠቀምና የአየር ንብረት ብክለትና የነዳጅ ወጪን ለመቀነስ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ወደ ገበያ ለማስገባት እየተሰራ ነው።

እስከ አሁን ባለው 100ሺህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን አንስተው በአስር አመት ውስጥም 500ሺህ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት መታቀዱን ተናግረዋል።


ተሽከርካሪዎቹ ኃይል የሚሞሉበት የቻርጂንግ ማሽኖች እየተተከሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ጤናማ ትራንስፖርትና መሰረተ ልማት እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ስማርት ሲቲ ለመገንባት በሚከናወኑ ተግባራት ግማሽ በላይ ድርሻ ያለው ስማርት ሞቢሊቲ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አስረድተዋል።

የከተማዋን ትራንስፖርት ተወዳዳሪ ለማድረግ መንገዶችን የማስፋት፣ ማቋረጫዎች፣ የእግረኛ መንገዶችና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በከተማዋ የብዙሃን ትራንስፖርትን ለማስፋት በተለይ የኤሌክትሪክ አውቶብሶችን ቁጥር በስፋት ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሁሉም ከተሞች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገልግሎትን ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑንና ክልሎችም እቅዱን ለማሳካት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ በበኩላቸው በኮሪደር ልማት ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ትራንስፖርት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ግንባታን የማዘመን ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በከተማ አስተዳደሩ 100 የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ግዢ መፈፀሙንና በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የትራንስፖርት ዘርፍ ሃላፊ ብርሃኑ ጌቦ(ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በብዛት መግባታቸውንና የቻርጅ መሙያ ማሽኖች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሐረሪ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ ዳይሬክተር ኢንጂነር በቀለ አንጊያ በከተማዋ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት የትራንስፖርት ዘርፉን የማዘመን ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከሚያቀርቡ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

የሲዳማ ክልል መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ታምሩ ታፌ በበኩላቸው በክልሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.