የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
የአፍሪካ ህብረት

<p>የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የህግ ማሻሻያዎችና የድጋፍ ስራዎች ይጠናከራሉ</p>

Jan 15, 2025

IDOPRESS

ጋምቤላ፤ ጥር 6/2017(ኢዜአ)፡- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የህግ ማሻሻያዎችና የድጋፍ ስራዎች እንደሚጠናከሩ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን(ዶ/ር) ተናገሩ።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በጋምቤላ ከተማ ሲያካሂድ የነበረው 12ኛው የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት የጋራ ጉባኤ መድረክ ማምሻውን ተጠናቋል።


የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን(ዶ/ር)፤ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የህግ ማሻሻያዎችና የድጋፍ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።

በተለይም መንግስት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ በሚያሻሽሉ የልማት ስራዎች ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የፖሊሲና የህግ ማሻሻያዎች ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለልማትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸውን ሚና እንዲወጡ ሚኒስቴሩ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ሞላ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያከናውኗቸው የልማት ስራዎች በተናበበና በተቀናጀ መልኩ ለማስኬድ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን ልናጠናክር ይገባል።

በተለይም የፌዴራልና የክልል የመንግስት ተቋማት ድርጅቶቹ ለመተግበር ያቀዷቸውን ፕሮጀክቶች በአግባቡ ማከናወናቸውን በመከታተል ረገድ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የጋራ ጉባኤው በአፈፃፀም ሂደት የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ጥንካሬዎችን ለማስፋትና ክፍተቶችን ለማረም አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

ጉባኤው ባለፉት አራት ወራት በሁሉም ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተከናወኑ የልማት ስራዎች ዙሪያ ውይይት በማድረግ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጧል።

በጋራ ጉባኤ ላይ የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት፣ የፍትህ ቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በነገው ዕለትም ተሳታፊዎች በጋምቤላ ክልል በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ የልማት ስራዎችን እንደሚጎበኙ የድርጊት መርሀ ግብሩ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.